7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከእስከ አሁኑ በበርካታ መመዘኛዎች የተሻለ ሆኖ ተጠናቋል- ምሁራን

AMN – ግንቦት 27 / 2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ታሪክ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በበርካታ መመዘኛዎች የተሻለ ሆኖ መጠናቀቁን ምሁራን ገለጹ፡፡

ምሁራኑ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በራሱ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ የቻለበት ነው፡፡

የሥነ- መንግስት ምሁሩ ዋቅቶሌ ዳዲ(ዶ/ር) ፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በምርጫ ብቻ ስልጣን መተላለፍ እንዳለበት መልዕክት ያስተላፈበት ነው ብለዋል፡፡

በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃ/ማርያም በበኩላቸው፣ ምርጫው ከግብፅ እና ከናይጄሪያ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህዝብ ተሳትፎ ከተደረገባቸው የአፍሪካ ምርጫዎች መካከል የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በምርጫው እለት መሳተፉ ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንጻር እጅግ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በተለይም አሳታፊና አካታች ሆኖ መጠናቀቁ ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ለምትጥረው የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ መሰረትን ጥሎ ያለፈ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ምርጫው ኃላፊነትን የሰጠ፣ ፍላጎትን ያሳወቀ እና ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንጻርም የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፋንታ በሚመለከት ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደት ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ በተለይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቅሰው፣ ይህም የተቋማት ግንባታ ሂደት ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

በቀጣይ የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ የሚመረጠው ፓርቲም ልክ እንደ ምርጫ ቦርዱ ሁሉ ህዝብ የሚተማመንባቸውን፣ ሀገርን የሚያሻግሩ ተቋማትን እንዲገነቡ የቤት ስራን የሰጠ ነውም ብለዋል።

በየሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review