AMN- ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የብዙ ባሕላዊ ሀብቶችና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች ባለቤት የሆነች፣ ኅብረ ብሔራዊት ሀገር መሆኗ ይታወቃል። በቋንቋ ሀብት የላቀች፣ በባሕል የደመቀች፣ በመንፈሳዊና ሰው-ሠራሽ ቅርሶች የናጠጠች እንዲሁም አኩሪ ታሪክ ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን፤ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ይገኛል።
ጥበብ ለጥበብነቷ ብቻ ሳይሆን ሀገርን የማልማትና የመገንባት ታላቅ ተልዕኮ እንዳላት ይታመናል።
ኪነ ጥበብ በሥነ ውበት አጊጣ ለእውነት ስትቆም ለሕይወት መድህንና ለነፍስ ፍሥሐ ትሆናለች።
በመሆኑም የባሕል፣ የኪነ ጥበብና የቅርስ ጥበቃ ሥራዎች የሕዝቡን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉና የአንድነት መሠረት እንዲሆኑ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው።

ባለፉት ዓመታት የባሕልና የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሕጋዊ መሠረት እንዲኖራቸው ለማስቻል ተገቢ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል።
ከእነዚህም መካከል የጥበባት ረቂቅ ፖሊሲ፣ የፊልም ፖሊሲ፣ የቋንቋ ፖሊሲና የባሕል ፖሊሲ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ፖሊሲዎች የሕዝቡን አብሮነት የሚያጎሉና ለወል ትርክት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።
በተለይም የቋንቋ ፖሊሲው የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በቋንቋቸው እንዲማሩና እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ 54 ሺህ በላይ ከያንያን ጋር ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸው ባለሙያዎች ጥበባቸውን ለብሔራዊ ጥቅም እንዲያውሉ መንገድ ከፍቷል።
በቅርስ ጥበቃ ረገድም ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማስገኘት በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል። የጊፋታ፣ የፊቼ ጨምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ የመስቀል፣ የጥምቀትና የሸዋሊድ በዓላት በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገቡ ተደርጓል።
ለረዥም ጊዜ ጥገና ሳይደረግላቸው የቆዩ ከ28 በላይ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች በከፍተኛ በጀት እንዲታደሱ ተደርጓል።

ይህም የሀገራችንን ገናና ማንነት ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ ከ30 በላይ ቋንቋዎች ዲጂታይዝድ እንዲሆኑ በማድረግ ዜጎች በቀላሉ እንዲማሯቸውና የእህትማማችነት ዕሴት እንዲጎለብት ተደርጓል።
የመሠረተ ልማት ግንባታን በተመለከተ፣ በገበታ ለሀገርና በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የኪነ ጥበብ ማዘውተሪያዎች እንዲካተቱ ተደርጓል።
በዚህም መሠረት 53 አንፊ ቴአትሮች፣ 39 ሲኒማ ቤቶችና 110 ፕላዛዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅም “ኪን-ኢትዮጵያ” የተሰኘ የባሕልና ጥበባት ጉዞ በተለያዩ ሀገራት ተከናውኗል።
ለሀገራቸው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጥበብ ባለውለታዎችም የመታሰቢያ ሐውልቶች ተገንብተውላቸዋል።
ይህ ተግባር መንግሥት ለባለሙያዎች ያለውን ክብርና ዘርፉን ከወቀሳ ወደ ሙገሳ ለማሸጋገር ያለውን ጽኑ አቋም ያሳየበት ነው።
ኪነ ጥበብ በዘመናዊና ባሕላዊ መልኳ ተቀናጅታ ኅብረ-ብሔራዊነት እንዲያብብ፣ ልማትና ዲሞክራሲ እንዲፋፋ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
መንግሥት የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም፣ የባሕልና የኪነ ጥበብ ሀብቶቻችን ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተርፉ በስትራቴጂክ መንገድ ይሠራል። የኢትዮጵያን ብዝኃነት እንደ ውበትና እንደ ጥንካሬ በመጠቀም፣ በጥበብ የተገነባችና የበለፀገች ሀገርን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።