በአምስት አመታት አንድ ጊዜ የሚገኘውን የመምረጥ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ሕገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችን ስለሆነ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል – የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች

You are currently viewing በአምስት አመታት አንድ ጊዜ የሚገኘውን የመምረጥ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ሕገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችን ስለሆነ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል – የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች

AMN-ግንቦት 23/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እያካሄደች በምትገኘዉ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች ነገ በይፋ ድምጽ ይሰጣሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በዚህ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በመሳተፍ ከማለዳ ጀምሮ ድምጻቸዉን ለመስጠት መዘጋጀታቸዉን ለኤኤምኤን ተናግረዋል፡፡

ድምፃችን ትልቅ ዋጋ ስላለው በምርጫው እለት በንቃት ለመሳተፍ እና የሚበጀንን ፓርቲ በካርዳችን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡

በአምስት አመታት አንዴ የሚገኘውን የመምረጥ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ሕገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንደሚጠቀሙ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

ለዚህም የወሰዱትን የመራጭነት ካርድ በምርጫው እለት ድምጻቸውን በመስጠት እንደሚጠቀሙበት አረጋግጠዋል።

ምርጫ በአንድ ሀገር የዴሞክራሲያዊ ሥርአት ከሚጎለብትባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው እንደመሆኑ ይህን ዕድል ለመጠቀም የድምጽ መስጫ እለቱን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዕለቱን ለሀገርና ለህዝብ በተሻለ ይሰራል ብለን ላሰብነው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻችንን እንሰጣለን ያሉት ነዋሪዎቹ ሌሎችም የወሰዱን የምርጫ ካርድ እንዲጠቀሙበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ምርጫውን ለማሳለጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን እያሰራጨ ይገኛል።

ለምርጫው አስፈላጊ የሆኑት ግብዓቶች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች፣ የመራጮች መዝገብ፣ የድምጽ መስጫ ኮሮጆና የተለያዩ ቅጻ ቅጾች ናቸው እየተሰራጩ የሚገኙት፡፡

የቁሳቁስ ስርጭቱ በጥንቃቄና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በጸጥታ ሃይል ታጅቦ እየተጓጓዘ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽ እየሆነ ይገኛል።

የነቃ ተሳትፍ የሚደረግበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 54 ሚሊዮን 57 ሺ ዜጎች ድምፃቸውን የሚሰጡ ሲሆን የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል።

55 የሀገር ውስጥ እና 2 የውጭ ተቋማት ምርጫውን የሚታዘቡ ሲሆን፣ 52 ሺህ ምርጫ ጣቢያዎች እና 359 ሺ የምርጫ አስፈፃሚዎች በእለቱ አገልግሎት ይሰጣሉ።

59 አባላት ያሉት የአፍሪካ ህብረት እና 26 አባላት ያሉት የኢጋድ የታዛቢዎች ቡድን አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣56 የሀገር ውስጥ እና 12 የውጭ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ምርጫውን እንደሚዘግቡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review