AMN – ግንቦት 13/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ፣ የሰላም ሰራዊት እና የደንብ አስከባሪዎች እንዲሁም የሸገር ከተማ የሲቪል ጥበቃ (ጋቻና ሲርና) አባላት በጋራ የሚከናወነውን የስምሪት ተግባር ተቀብለዋል።
በዚህ መርሐ ግብር ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማን ጨምሮ የፌደራል፣ የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተሞች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመደረኩ መልዕክት ያስተላልፉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፣ “ለትላንትናው ስራችሁ ክብር ይገባችኋል፤ ወደፊትም የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት መስራታችሁን መቀጠል አለባችሁ ሲሉ አስገንዝበዋል።
በተለይም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላምና በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ከፍተኛ ሚና እንዲወጡም አደራ ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን በመጠበቃችሁ ልትኮሩ ያሉ ሲሆን፣ የሁለቱን ከተሞች ዘላቂ ሰላም ለማስቀጠል ይበልጥ በማጠናከር መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፣ ዓለም ያደነቀውን ፈጣን ልማት ይበልጥ ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ የበለፀገች ሀገር ለልጆቻችን ለማስረከብ ሰላምን በዘላቂነት ማስቀጠል የግድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፣ ሁለቱ ከተሞች የተለያዩ ወንጀሎችንና የጸረ ሰላም-ኃይሎችን እንቅስቃሴ በጋራ ሲከላከሉና ሲቆጣጠሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ከዚህ በኋላም መደበኛ መዋቅር በማዘጋጀት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በጋራ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ የአደባባይ በዓላት በአዲስ አበባ ያለ ምንም ችግር መከናወን መቻላቸውን ጠቁመው፣ የተጀመረው የተቀናጀ አሰራር በቁርጠኝነት እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ፣ ሰላም የሁሉም ዜጋ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሁለቱ ከተሞች ማህበረሰብና የጸጥታ መዋቅር ቅንጅት ማንኛውም አካል ወንጀል ፈጽሞ የትም ሊደበቅ እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የሁለቱ ከተሞች በተለይም የአጎራባች ክፍለ ከተሞች የጸጥታ መዋቅር ቅንጅት እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና በጋራ በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በመሐመድ ቶፊቅ
Boost th