AMN ግንቦት 27/2018

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም መመዘኛዎች ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ የምርጫ ሂደት መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ።

አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱንና የዜጎችን ተሳትፎ በተመለከተ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም የምርጫ ሂደቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ በርካታ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በሃሳብ ክርክር የዘለቀና ድምፅ ለመስጠትም በርካታ ዜጎች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በድምጽ አሰጣጡም ዜጎች ዝናብ፣ብርድና ፀሃይ ሳይበግራቸው ከማለዳ እስከ ሌሊት ድምፅ የሰጡበት ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁሉንም አሳታፊ ባደረገ መልኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ምክር ቤቱ በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በመሆኑም ምርጫው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ሂደቱ እንደ አጠቃላይ የተሳካ መሆኑን ገልጸው፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መፎካከሩ እንዳለ ሆኖ በቀጣይ ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ በጋራ መቆም እንደሚገባም መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡