AMN- ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ እስከ 28 ቀናት የሆናቸው ጨቅላ ህፃናት ከአዋቂዎችም ሆነ ከሌሎች ህፃናት በተለየ መልኩ ለአደጋ የመጋለጥና በቀላሉ የመጎዳት እድላቸው ከፍተኛ ነው።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት መረጃዎች መሰረት፣ 80 በመቶው የሚሆነው የጨቅላ ህፃናት ሞት አስቀድሞ መከላከል በሚቻሉ ምክንያቶች የሚከሰት ነው።
በአበበች ጎበና የእናቶችና የህፃናት ሆስፒታል የህፃናት ስፔሻሊስት ዶክተር ኤርሚያስ ጌታቸው የጨቅላ ህፃናት ሞት መንስኤዎች፣ ምልክቶችና መፍትሄዎቻቸውን በተመለከተ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ለወላጆች ጠቃሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጨቅላ ህፃናት ሞት ዋና ዋና ምክንያቶች፡-

የጨቅላ ህፃናት ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት ከሚሆኑት እና 80 በመቶው የሚሆነውን ድርሻ ከሚይዙት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል፡-
ቀድሞ መወለድ (Prematurity): አንድ ህፃን መደበኛውን የእርግዝና ጊዜ አጠናቆ መወለድ ያለበት በ9 ወር ከ10 ቀን ቢሆንም፤ ከዚህ ጊዜ ቀድመው (በ7 ወይም በ8 ወር) የሚወለዱ ህፃናት የአካል ክፍሎቻቸው በሚገባ ስለማይጠነክሩ ለሞት የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው።
የክብደት ማነስ፡- የጤናማ አዲስ የተወለደ ህፃን ትክክለኛ ክብደት ከ2.5 እስከ 4 ኪሎ ግራም ነው። ከ2.5 ኪሎ ግራም በታች የሆኑ፣ በተለይም ደግሞ ከ1.5 ኪሎ ግራም በታች የሚመዝኑ ህፃናት ከአዲሱ አካባቢ ጋር በቀላሉ የመላመድ ችግር ስላለባቸው ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ ናቸው።
ኢንፌክሽኖች፡- በተለይ በታዳጊ ሀገራት ህፃናት ለተለያዩ የኢንፌክሽን አይነቶች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ለህልፈት ይዳረጋሉ።
ታፍኖ መወለድ፡- ህፃናቱ በሚወለዱበት ሰዓት የኦክስጅን ወይም የሌሎች ነገሮች እጥረት ሲያጋጥማቸው ታፍነው ሊወለዱ ይችላሉ።
ወላጆች ሊያውቋቸው የሚገቡ የጨቅላ ሕጻናት የህመም ምልክቶች
የጨቅላ ህፃናት ህመም ምልክቶች ብዙ ጊዜ ግልጽ ላይሆኑና ሊያደናግሩ ይችላሉ።

በመሆኑም አንድ ጨቅላ ህፃን መታመሙንና በአስቸኳይ ወደ ህክምና መወሰድ እንዳለበት የሚያሳዩ ዋና ዋና ምልክቶች መካከል፣ ህፃኑ ጡት ለመጥባት ፍላጎት ማጣት ወይም ሙሉ በሙሉ ማቆም።
ቶሎ ቶሎ መተንፈስ ወይም የአተነፋፈስ ስርአት መዛባት፣ ባህሪ መቀየርና ሰውነትን ማንቀጥቀጥ እና እንደ ሜኒንጃይተስ ወይም የጭንቅላት ኢንፌክሽን ያሉ ህመሞች ሲኖሩ፣ የልብ ምት መዛባት በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የደም ዝውውር ሲቀንስ ሊከሰት ይችላል።
በህፃኑ ላይ ማንኛውንም አይነት የተለየ ለውጥ ሲመለከቱ ሳይዘገዩ በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ በምርመራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ለጨቅላ ህፃናት የሚደረጉ የህክምና እንክብካቤዎች፡-

ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ሲያጋጥሙ በሆስፒታል ውስጥ የሚከተሉት ህክምናዎችና ልዩ እንክብካቤዎች ይሰጣሉ የሚሉት ዶክተር ኤርሚያስ ቀድመው ለተወለዱና ክብደታቸው ላነሰ ህፃናት፣የራሳቸውን ሙቀት መጠበቅ ስለማይችሉ ክብደታቸው እስኪጨምር ድረስ በኢንኩቤተር ውስጥ ክትትል ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡
ሳንባቸው በሚገባ ስላልጠነከረ የአተነፋፈስ ችግራቸውን ለመቅረፍ ኦክስጅን ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ምግብ ቶሎ መቀበል ስለማይችሉ መጀመሪያ ላይ በግሉኮስ መልክ እየተሰጣቸው በሂደት ምግባቸው ከፍ ይላል ስላዚህ የአመጋገብ ክትትል ያስፈልጋቸዋል።

እናት ልጇን በጡቶቿ መካከል በማቀፍ፣ ወፍራም ልብስ አልብሳ የራሷን የሰውነት ሙቀት ለህፃኑ የምታስተላልፍበትና ክብደት እስኪጨምር ድረስ በሆስፒታል አልጋ ተሰጥቷት የምታጠባበት ፍቱን የህክምና ዘዴ ነው።
ለታፈኑና ኢንፌክሽን ላለባቸው ህፃናት ደግሞ ትክክለኛውን ሙቀት እንዲያገኙ ማድረግ እና የኦክስጅን ድጋፍ መስጠት።
መታፈኑን ላመጣው ኢንፌክሽን የሚሆኑ የአንቲባዮቲክስ ህክምናዎችን መስጠት።
የኩላሊት ምርመራ በማድረግ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ እና ችግሩ ከበድ ካለ ደግሞ የመተንፈሻ ማሽን መጠቀም።
ተጨማሪ መፍትሄዎች
የጨቅላ ህፃናትን ሞት በዘላቂነት ለመቀነስ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ቅድመ-እርግዝና እና የእርግዝና ጊዜ ክትትል ነው።
ከእርግዝና በፊት፣ አንዲት እናት ለማርገዝ ስታስብ አስቀድማ ከሀኪም ጋር መማከርና መታከም ያለባቸውን ነገሮች ቀድማ መጀመር ይኖርባታል።
ከእርግዝና በኋላ፣ እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ጥብቅ የሆነ የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።
ይህ ሲሆን እንደ ደም ማነስና ኢንፌክሽን ያሉ ቀድሞ መወለድን የሚያስከትሉ ችግሮችን አስቀድሞ በማከም ቀድመው የሚወለዱ ህፃናትን ቁጥርና የጨቅላ ህፃናትን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል።
በፍሬሕወት ብርሃኑ