የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዲፕሎማቶች የሁኔታዎች አዝማሚያና የቀውስ ወቅት ዲፕሎማሲ አስተዳደር ስልጠና ሰጠ

You are currently viewing የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዲፕሎማቶች የሁኔታዎች አዝማሚያና የቀውስ ወቅት ዲፕሎማሲ አስተዳደር ስልጠና ሰጠ

AMN- ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሁኔታዎች፣ አዝማሚያ ትንተና እና የቀውስ ወቅት ዲፕሎማሲ ላይ በዋናው መሥሪያ ቤት እና በተለያዩ የዓለም ክፍል ለሚገኙ ከ60 በላይ ዲፕሎማቶች የሰጠው ስልጠና ተጠናቋል።

ስልጠናው በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው ዓለም አቀፍ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በብቃት ለማስጠበቅ የዲፕሎማቶችን ዕውቀት፣ ክህሎት እና ሙያዊ ብቃት ለማጎልበት ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ የዘመኑ ዲፕሎማሲ ሙያውን በሳይንሳዊና በዘመናዊ አቀራረብ እንዲመራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ባለሙያዎች በተከታታይ ስልጠና፣ በዕውቀትና በክህሎት መደገፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም መሰል ስልጠናዎች ወደፊት ለሁሉም የሚኒስቴሩ ሰራተኞች እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ስልጠናው የሚኒስቴሩ የሦስት ዓመት የአቅም ግንባታ መርሐ ግብር አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሰራተኞችን ሙያና ክህሎት በማዳበር ከሀገሪቱ ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተጣጣመ ቀጣይነት ያለው የሰው ሀብት ልማት ስርዓት ለመገንባት የታለመ መሆኑን አብራርተዋል።

የስልጠና መርሐ ግብሩ የሚኒስቴሩን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር ብቁና ዝግጁነትን የተላበሰ የሰው ኃይል ለማፍራት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ሥልጠናውን ላጠናቀቁ ሰራተኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review