በልዩ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሂደት ነገ ሰኔ 2 ይከናወናል

You are currently viewing በልዩ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ድምፅ የመስጠት ሂደት ነገ ሰኔ 2 ይከናወናል

AMN ሰኔ 1/2018

በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና በወታደራዊ ካምፖች በሚገኙ ልዩ ጣቢያዎች ነገ በልዩ ሁኔታ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጠት ሂደት እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ምርጫ ቦርድ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጠት ሂደት ማስፈጸሙን አውስቷል።

በአሁን ሰዓት ቦርዱ ከምርጫ ክልል ጽህፈት ቤት ወደ ቦርዱ ማዕከል በመምጣት ላይ ያሉ ውጤቶችን የማረጋገጥ፣ የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ውጤቶች የመመርመር እንዲሁም የተረጋገጡ ውጤቶችን ወደ መረጃ ቋት የማስገባት ሥራ ላይ እንደሚገኝም አመልክቷል።

በተጨማሪም በፖለቲካ ፓርቲዎችና በግል ዕጩዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በሕግ ባለሙያ ጉባዔ አማካኝነት የማደራጀትና ምሥክር የመሥማት ሥራ እያከናወነ ነው።

በቀጣይም በተጠቀሰው ሂደት ያለፉ ውጤቶች ለቦርድ ውሣኔ በማቅረብ እና በማፀደቅ በሕጉ መሠረት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ቦርዱ አስታውቋል።

ቦርዱ “በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 17” በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና በወታደራዊ ካምፖች ልዩ ጣቢያዎችን በማቋቋም የካምፑ ነዋሪዎችን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ እንዲሣተፉ በመራጭነት መመዝገቡ ይታወቃል።

በመሆኑም በካምፖቹ በመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች ድምፅ የመስጠት ሂደት ነገ እንደሚከናወን ቦርዱ በመረጃው አመልክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review