ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተመራጮች ሀገራቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቀረቡ

AMN – ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቅንና ይፋዊ የውጤት መግለጫን ተከተሎ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በምርጫው ያሸነፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በታማኝነትና በዕውቀት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ፕሬዚዳንቱ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አበርክቶ ላደረጉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት፣ ለጸጥታ መዋቅሩ እንዲሁም ከ64 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ታዛቢዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያሳየ የመጣውን ተቋማዊ ዕድገትና የአመራር ብቃትም አድንቀዋል።

በተለይም ተቋሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በምርጫ ሥርዓቱ ውስጥ በማላመድና አሠራሩን ለማዘመን የወሰዳቸውን በጎ እርምጃዎች በምሳሌነት አንስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸው፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 56 የፖለቲካ ሥልጣንን ድንጋጌ በሚያዝዘው መሠረት፣ ሕዝቡ “ይመራኛል” ያላቸውን አካላት በነፃነት መምረጡን አስታውሰዋል።

በመሆኑም በፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ አሸንፈው ለተመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፣ የምትታወሱት ጥፋትን በማወጅ ሳይሆን በዕድገትና በዕውቀት እንዲሆን፣ ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ በታማኝነት፣ በቅንነት፣ በንጹህ ሕሊና እና በዕውቀት ልታገለግሉ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review