ከቆሻሻ መጣያነት ወደ ውብ የመዝናኛ ማዕከልነት የተለወጠው የዕንጦጦ ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ የሥራና የቱሪዝም ተስፋ ይዞ ብቅ ብሏል

You are currently viewing ከቆሻሻ መጣያነት ወደ ውብ የመዝናኛ ማዕከልነት የተለወጠው የዕንጦጦ ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ የሥራና የቱሪዝም ተስፋ ይዞ ብቅ ብሏል

AMN – ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

ትላንትና የቆሻሻ መጣያ የነበረው የቀበና አካባቢ ዛሬ ላይ በርካቶች መንፈሳቸውን የሚያድሱበት ውብ የመዝናኛ ስፍራ በመሆን አዲስ የአዲስ አበባ ገጽታ ሆኖ ብቅ ብሏል። በውስጡ በርካታ መሠረተ ልማቶችን ያካተተው የዕንጦጦ ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ለአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለሴቶችና ለታዳጊ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድልና አዳዲስ የገቢ ምንጮችን እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት የቀበና አካባቢ ሙሉ በሙሉ ገጽታውን መቀየር የቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የነዋሪዎችና የጎብኚዎች ተመራጭ የመዝናኛ ማዕከል ለመሆን በቅቷል።

አካባቢው ካለው ውበትና አዲስ ገጽታ የተነሳ በርካታ ወጣቶች የፎቶግራፍ ጥበብን ጨምሮ በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ኤ ኤም ኤን ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል የፎቶግራፍ ባለሞያው ደስታው አለሙ ተናግሯል።

ልማቱ ካካተታቸው አዳዲስና ሳቢ መሠረተ ልማቶች መካከል የጀልባ ጉዞ፣ የተለያዩ የዥዋዥዌ መጫወቻዎችና የልጆች የመዝናኛ ስፍራዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ይህ የወንዝ ዳርቻ ሪዞርት ለከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን እንደ ቱሪስት መዳረሻነትም በማገልገል ላይ መገኘቱን ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ታምራት ያድን ለኤ ኤም ኤን ገልጿል።

በተለይም አሁን ላይ የክረምት ወቅት በመሆኑና ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው፣ ታዳጊዎችና ልጆች ጊዜያቸውን በደስታና በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚያሳልፉበት አስተማማኝ የመዝናኛ እና የመጫወቻ ስፍራ መገንባቱን ነዋሪዎች አንስተዋል።

በመዲናችን አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘወተረ የመጣውን “የስኬት” ስፖርት ለማስተናገድ የሚያስችል ሰፊና ዘመናዊ የስፖርት ስፍራ በዚህ በቀበና ልማት ውስጥ ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ተጠቁሟል።

ይህ አደረጃጀት ታዳጊዎች የክረምት እረፍታቸውን በቤት ውስጥ ከማሳለፍ ይልቅ ወደ ማዕከሉ በመምጣት ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉና እንዲዝናኑ ምቹ ዕድል ፈጥሯል።

ይህ የተከናወነው ታላቅ ልማት ለዚህ ትውልድ የተሰጠ ትልቅ ገጸ-በረከት መሆኑን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ የተገኘውን ውበትና ቅርስ ዘላቂ ለማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ ልማቱን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም አረንጓዴ ተክሎችን በመትከል፣ ሳሮችን በመንከባከብና በወንዙ ውስጥ ሌላ ቆሻሻ እንዳይገባ በጋራና በተደራጀ መልኩ በመከላከል ረገድ የሁሉም ነዋሪ ንቁ ተሳትፎና ግዴታ መሆኑ ተገልጿል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review