AMN- ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም

አንዳንድ የሕይወት አጋጣሚዎች ሰውን ለጥቂት ጊዜ ሳይሆን ለዓመታት ይፈትኑታል።
የ18 ዓመቷ ትዕግስት አበበ የልጅነት አደጋ ያመጣውን የ18 ዓመታት ስቃይ ዛሬ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በተደረገላት ተአምራዊ ህክምና እፎይታን አግኝታለች።

ከ18 ዓመታት በፊት በደቡብ ወሎ የስድስት ወር ህፃን ሳለች ከፍራሽ ላይ ተንከባላ በእሳት ላይ በመውደቋ በእጇ ላይ ከባድ የቃጠሎ ጠባሳና መጨማደድ ደረሰባት።
በወቅቱ ተገቢውን የህክምና እድል ባለማግኘቷ የተነሳ እጇን መዘርጋት፣ ማጣጠፍ፣ የፈለገችውን ነገር በነፃነት መያዝ እና እንደሌሎች ሰዎች በእጇ ተጠቅማ የዕለት ተዕለት ተግባሯን ማከናወን አልቻለችም ነበር።
18 ዓመታት ሙሉ እጇን ብቻ ሳይሆን በልቧም የመተማመን ማነስን አብራ ተሸክማ አደገች።
ለዓመታት የቆየውን ይህንን ከባድ ችግር ለመቅረፍ ትዕግስት ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ መጣች።

በዶ/ር ዳግማዊ ገረመው የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ሀኪምና ረዳት ፕሮፌሰር የተመራው የህክምና ቡድን፣ የቃጠሎውን ከፍተኛ ጉዳት በጥንቃቄ መርምሮ ባደረገላት የላቀ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና የእጇን ገደብ ሙሉ በሙሉ አሻሽሎታል።
እጇን ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ መዘርጋትና ማጠፍ ጀመረች፣ ማንኛውንም ነገር ጨብጦ መያዝ እና ሰውን በእጅ መጨበጥ ቻለች፣ ከሁሉም በላይ አደጋው በሕይወቷ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በአዲስ ተስፋ ተተካ፡፡
ዶ/ር ዳግማዊ ገረመው እንደገለጹት፤ “የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና የአካል ገጽታን ለማስተካከል ብቻ የሚደረግ ሳይሆን፣ ታካሚዎች ለዓመታት የተሸከሙትን የአካል ገደብ በማሻሻል ወደ ተሻለ የኑሮ ጥራት እንዲመለሱ የሚያስችል የሕይወት ለውጥ ነው” ብለዋል።
ይህ ስኬት የህክምና እውቀት፣ የሙያ ትጋት እና የታካሚ ጽናት ተደምረው የፈጠሩት ትልቅ ድል መሆኑን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ የ18 ዓመቷ ትዕግስት የትናንቱን ህመም ትታ የነገውን ሕይወት በተስፋ ትገነባለች፡፡