AMN- ሰኔ 28/2018 ዓ.ም
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ፤ ተቋሙ መረጃዎችን በመስጠት፣ በማስተማር እና በማዝናናት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገለጹ፡፡
የትውልድ ድምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ”አሸናፊ ትውልድ” የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ፤ ”አሸናፊ ትውልድ” የሩጫ ውድድር አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የትውልድ ድምፅ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ተቋሙ ለተመልካች እና አድማጭ ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን በኤ ኤም ኤን፣ በኤ ኤም ኤን ፕላስ፣ በኤፍ.ኤም 96.3፣ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ እና በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች እያገለገለ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በመንግስት እና በህዝብ መካከል እንደ ድልድይ በመሆን እያገለገለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ “ማህበረሰቡ ሚዲያውን እንዲከታተልና መረጃዎችን እንዲያገኝ እንዲሁም እንደ ‘ዋርካ’ ባሉ የህዝብ አገልግሎት ፕሮግራሞች ላይ በንቃት ተሳታፊ እንዲሆን እንጋብዛለን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የ“አሸናፊ ትውልድ” የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር መነሻውን ዓድዋ ድል መታሰቢያ መዳረሻውን ደግሞ ቀበና አድርጓል፡፡
በትዝታ መንግስቱ