የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በቅንጅት የተሰራው ወንጀልን የመከላከል ሥራ ስኬታማ መሆኑን ገለጸ

AMN- ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል እንዲቻል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ስኬታማ ሥራ መሰራቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ከማዕከል እስከ ወረዳ ከሚገኙ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ዳይሬክቶሬቶች ጋር የግምገማ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፤ በአዲስ አበባ የወንጀል ምጣኔ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 47 በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በማካሄድ አዲስ አበባን የሁነቶች ማዕከልና የቱሪስቶች መናኸሪያ መሆኗን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

ከተቋም ግንባት ሥራዎች አኳያ የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና በመስጠት ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሥራዎች የተሰሩበት ዓመት መሆኑን ጠቅሰው፣ የተቋሙን ራዕይ የሚረዳና የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያቀላጥፍ ሰራተኛ በመፍጠር ረገድ በዓመቱ ስኬታማ ሥራ ተሰርቷል ሲሉም ገልፀዋል።

የሰላም እሴትን ከመገንባት አኳያ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ የመዲናዋን ሰላም ማስጠበቅና ማስቀጠል መቻሉን ወ/ሮ ሊዲያ አንስተዋል፡፡

የሰላም ሰራዊት አደረጃጀትን በተመለከተ በዓመቱ ከ44 ሺህ በላይ አዲስ የሰላም ሰራዊት አባላትን በመመልመልና በማሰልጠን ወደ ሰላም ማስጠበቅ ተግባር እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

መረጃን ከስሩ ማጥራት ብልሹ አሰራርን መከላከልና ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል እንዲቻል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ስኬታማ ሥራ የተሰራበት ዓመት እንደነበርም አስረድተዋል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review