የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላልተካተቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታጣቂዎች ጥሪ አቀረበ

AMN – ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) እስከ አሁን በምክክሩ ሂደት ላልተካተቱ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታጣቂዎች አዲስ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የምክክሩ ሂደት ስኬታማ መሆን ቀደም ሲል ያልነበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እየሳበ መሆኑን እና አሁንም መካተት የፈለጉትን በማካተት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ታሪካዊ የምክክር ሂደት፣ ባለፉት ቀናት ለአራት ሺህ የምክክሩ ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ ስልጠናዎችንና ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።

ተሳታፊዎቹ በስምንት የአጀንዳ ክፍሎች ተከፋፍለው ሥነ-ዘዴዎችን፣ የውሳኔ አሰጣጥ አካሄዶችንና በሀገራዊ መግባባት ሂደት ውስጥ ሁሉም ክልሎች እኩል መስተጋብር ፈጥረው የህልውና ጥያቄዎቻቸው በትክክል የሚመለሱበትን ስልቶች በሚገባ ተወያይተውባቸዋል።

ኮሚሽኑ ቅዳሜና እሁድን በመጠቀም እስከ አሁን ያጋጠሙ ትናንሽ ክፍተቶችንና የተዋንያን አቀማመጥ አለመመጣጠኖችን በተለይም የሃይማኖትና የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፍን የማስተካከልና የማጥራት ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር ያከናውናል ብለዋል።

ይህ ተግባር ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ ሁሉም ተሳታፊዎች የተጣለባቸውን ሀገራዊ አደራ ለመወጣት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ገልጸዋል።

ሚዲያዎችም መረጃዎችን ታች ድረስ በማድረስ ላደረጉት ሥራ ምስጋና ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ኅብረተሰቡ ስለ ሀገራዊ ምክክሩ በደንብ እንዲገነዘብ መረጃዎች በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review