የአዲስ መሶብ ዲጂታል አገልግሎት እንግልትን በመቀነስ የፍትሃዊነት ጥያቄዎችን እየመለሰ ነው

AMN – ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በዘርፉ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከመፍታት ባለፈ፣ የሕዝብን እርካታና በአገልግሎቱ ላይ ያለውን አመኔታ የሚያረጋግጥ ዘመናዊ ተቋም እየገነባ መሆኑን አስታወቀ።

የአዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደሳለኝ ተረፈ ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት ፣ ዲጂታላይዜሽን በመጠቀም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይታይ የነበረውን እንግልትና የቢሮክራሲ ችግር የመቅረፍ ስራ እየተሰራ ነው።

ኢንጂነር ደሳለኝ እንደገለጹት፣ ዲጂታላይዜሽን የዜጎችን የጊዜ ብክነት፣ የፋይል መጥፋት እና ተደጋጋሚ ምልልስን በማስቀረት አገልግሎቱን ፈጣንና ፍትሃዊ አድርጎታል።

መንግስት የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ፣ አሮጌውን የአሰራር አስተሳሰብ በመስበር ዘመናዊ እና ግልጽ አሰራርን መዘርጋት ችለናል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 11 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ተንቀሳቃሽ አገልግሎቶችንም ጨምሮ ተደራሽነቱ እየሰፋ ይገኛል።

በአሁኑ ሰዓት ከ25 በላይ ተቋማት ተካተው ከ150 በላይ አገልግሎቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ በቀጣይም ተጨማሪ ተቋማትን በማካተትና የማዕከላቱን ቁጥርና አቅም በማሳደግ ተደራሽነቱን የማስፋት ስራ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ እየታየ ያለው ለውጥ የሕዝብን አመኔታ እያደሰ መምጣቱን የጠቆሙት ኢንጂነር ደሳለኝ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል አቅም እየገነባን ነው ብለዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ፣ ቀደም ሲል የነበሩትን የአገልግሎት መጓተትና የፍትሃዊነት ጥያቄዎችን በመመለስ፣ ለዜጎች ቀልጣፋና ተዓማኒነት ያለው የመንግስት አገልግሎትን እውን እያደረገ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review