AMN ሐምሌ 15/2018

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ በጀግንነትና በጽናት የሚታወቅ የሰላማችን መሠረትና የሕያውነታችን አምባ የሆነ ታሪካዊ ተቋም ነው።
ሠራዊቱ የሕብረ ብሔራዊ አንድነት ምሳሌ በመሆን ሀገር የምትባለውን ታላቅ ምስል በአንድነት አቅፎ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በደሙና በአጥንቱ አስከብሮ አቆይቷል።

ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈታኝ ሁኔታዎችን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በድል ያለፈ እንዲሁም እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ የወጣ ሠራዊት በመሆኑ ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለሁለንተናዊ እድገት ፈር ቀዳጅ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
የሠራዊታችን አሸናፊነትና ድል አድራጊነት የሚመነጨው ከገነባቸው ወርቃማ ተቋማዊ እሴቶቹ ነው። “ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም” የሚለው መርሁ የሕዝባዊነቱ መሠረት ሲሆን፣ በየትኛውም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ “ምንጊዜም የተሟላ ስብዕናን” ጠብቆ መጓዙ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ለዴሞክራሲያዊ እሴቶችና ለሰብዓዊ መብቶች ላለው ታማኝነት ማረጋገጫ ነው።

ችግሮችን በኃይል ሳይሆን በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ የሚያደርገው ጥረት ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቡን የሚያሳይ ሲሆን፣ በተሰማራበት ሀገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዳጆች ሁሉ ኃላፊነትን በመወጣት ፕሮፌሽናልነቱን አረጋግጧል።
ወታደርነት ሀገርን አስቀድሞ ውድ ሕይወትን መስዋዕት ማድረግ መሆኑን አምኖ የጥይት አረርን አልፎ በጥማትና በብርድ ሳይበገር የወደቀውን ጓዱን ደግፎ “ቅድሚያ ለሀገር” በሚል ጽኑ ፍቅር ዳር ድንበርን ያስከብራል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ለተራበው የሚያካፍል፣ ለጠላት ሳይቀር የሚራራና በሰላም ጊዜ በልማት ሥራዎች ላይ አሻራውን የሚያስቀምጥ እውነተኛ የሕዝብ አለኝታ ነው።

በመደመር መንግሥት ዓመታት የተካሄዱ ተቋማዊ ሪፎርሞች ሠራዊቱን በዘመናዊ አደረጃጀት በሥልጠና፣ በከባድ መሳሪያዎችና እንደ ድሮን ባሉ የላቁ ቴክኖሎጂዎች እንዲታጠቅ በማድረግ ቀጠናዊ የበላይነቱን አረጋግጠዋል።
ይህ ታሪካዊ የውጊያ ጥበብ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር የተቀናጀበት አቅሙ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጥበብ እና ከመረጃ መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሳይበር ምሽግ ጋር የተጋመደ ነው።

መከላከያ ሠራዊቱ የሀገር ሰላም እና የአንድነት ምሰሶ የኢትዮጵያ ሕልውና መገለጫ እና የሕዝብ አለኝታ ሆኖ የሀገርን ክብር መጠበቁን ቀጥሏል።
በአሁኑ ወቅትም ሠራዊቱ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ሴራ በመበተን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚጥሩ የጥፋት ኃይሎችን በመመከት እና ሕግን በሕጋዊ መንገድ በማስከበር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ጂኦግሪፊያዊ አቀማመጥ ለብዙ ኃያላን ሀገራት የፍላጎት ማዕከል ቢሆንም፣ መከላከያ ሠራዊታችን ማናቸውንም የውጭ ከበባና የውስጥ ባንዳዎች ሴራ ለመመከት ሌት ከቀን ይተጋል።
ሠራዊታችን ቁልፍ እሴቶቹን፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቱን እና ድል አድራጊነቱን እንደጠበቀ የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ደኅንነት በማስከበር ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ አቁሞ ወደ ላቀ የብልፅግና ከፍታ የሚያሸጋግር የማይበገር ተቋም ነው። – የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት