የግብፅ ሴራዎችና የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ጉዞ

You are currently viewing የግብፅ ሴራዎችና የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ጉዞ

AMN- ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ለአንዳንዶች የኢትዮጵያ እና የግብፅ ውዝግብ የጀመረው በቅርቡ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ይመስለን ይሆናል።

ነገር ግን እውነታው ከዚህ እጅግ የላቀ እና ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ ያለው መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ታሪክ እንደሚያወሳው በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት የግብፅ መሪዎች በተለይም ኬዲቭ እስማኤል ” ዓባይን የተቆጣጠረ ምሥራቅ አፍሪካን ይቆጣጠራል” በሚል እሳቤ፣ “የዓባይን ምንጭ ተቆጣጥሮ ታላቋን የግብፅ ኢምፓየር መመሥረት” የሚል ሕልም ነበራቸው።

ይሁን እንጂ ይህ ምኞት በሕዳር እና በመጋቢት ወራት 1868 ዓ.ም በጉንደት እና በጉራዕ ውጊያዎች በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ሽንፈትን አስተናግዶ ከሽፏል።

ጦርነቱ ሲያቅታቸው ኢትዮጵያ በውስጥ ግጭት እና በኢኮኖሚ ደካማ እንድትሆን የማድረግ እንዲሁም በኃይለኛ የቅኝ ግዛት ውሎች እ.አ.አ የ1929 እና 1959 ስምምነቶች የዓባይን ውሀ ለብቻ የመጠቀም ፖሊሲ መከተል ጀመሩ።

ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ነገሮች በከፍተኛ ሁኔታ ተቀይረዋል፤ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ዓባይ ላይ የገነባችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ አሁን ላይ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።

ይህም የትላንቱን “የዓባይን ውሀ ብቸኛ ተጠቃሚነት” ትረካ በይፋ ቀይሮታል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው መርህ “ማንም ሳይጎዳ በጋራ የመጠቀም” እንጂ የትላንቱን የቁጥጥር አስተሳሰብ አይደለም።

የዛሬዋ ግብፅ የገጠማት ፈተና ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል እንዲኖር በጋራ ከቆሙት የናይል ተፋሰስ ሀገራት በሙሉ ነው።

ከትናንት ስህተቷ መማርን ያልፈቀደችውና ለትብብር ዝግጁነት የሌላት ግብጽ፣ በቀጣናው ያሉ የግጭት ፈረሶችን በመዘወር የረባሽነት ሚናዋን ቀጥላለች፡፡

ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን በኃይልም ሆነ በዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ማስቆም አለመቻሉን ነው።

የዛሬው ዘመን የሚጠይቀው የትናንቱን የፖለቲካ ሴራ ማቆም እና የወደፊቱን የጋራ ዕድገትና ሰላም በእኩልነት መገንባት ብቻ ነው፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review