የኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የሕዝብን የኢኮኖሚ ትስስር በማሳለጥ የብልፅግና ድልድይ እየገነቡ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የሕዝብን የኢኮኖሚ ትስስር በማሳለጥ የብልፅግና ድልድይ እየገነቡ ነው

AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የሕዝብን የኢኮኖሚ ትስስር በማሳለጥ የብልፅግና ድልድይ እየገነቡ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር “ኢትዮጵያን የማገናኘት 75 ዓመታት፤ መንገዳችን ኃላፊነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩን በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ክብረ በዓሉ ስኬቶች በመዘከር የወደፊቱን ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ግቦች የሚታደሱበት አጋጣሚ ነው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ባለፉት 75 ዓመታት ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን የመፈጸም ከፍተኛ አቅም እየገነባ የመጣ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ዘላቂ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚጣጣሙና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያካተቱ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ የመንገድ መሠረተ ልማት እድገት የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማሳለጥ የብልፅግና ድልድይ እየገነባ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሕዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመሠረተ ልማት ግንባታው በይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው ሚኒስቴሩ ለአስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የቦርድ ሰብሳቢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አስተዳደሩ በ75 ዓመታት ጉዞው የሀገሪቱ ልማት ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን ከ180 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መድረሱን በመጠቆም በቅርብ ዓመታት ብቻ ከ44 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች በመገንባት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የመንገድ መሠረተ ልማት ሕዝቦችን ከማቀራረብ ባለፈ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያፋጠነ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን ናቸው።

የኢትዮጵያ የመንገድ አውታር መስፋፋት ተቋማዊ የቴክኖሎጂ አቅምን ከማሳደጉም በተጨማሪ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ለተቋሙ ስኬት መሠረት ለጣሉ የቀድሞ አመራሮች የመንገድ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መሐንዲሶች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review