ኢትዮጵያዊያን ታሪክ እየሰሩ ነው!

You are currently viewing ኢትዮጵያዊያን ታሪክ እየሰሩ ነው!

AMN- ሐምሌ17/2018 ዓ.ም

ምክክር እና ንግግር ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ባህል ባይሆንም እስከ ዛሬ ድረስ ግን በሃገር አቀፍ ደረጃ በጋራ መነጋገርና መመካከር ባለመቻሉ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶች ወደ ግጭትና ጦርነት እስከማምራት ደርሰዋል፡፡

በፖለቲካ ልዩነቶች ፣ በሃሰተኛ ትርክቶችና በይገባኛል ጥያቄዎች ምክንያት ከህይወት መጥፋት እስከ ንብረት መውደም የደረሱ ትላልቅ ጉዳቶችም ተከስተዋል፡፡

በወንድማማች ህዝቦች መካከል ሲነገሩ የነበሩ ሃሰተኛና የጥላቻ ንግግሮች በብሄር ብሄረሰቦች ፣ በሃይማኖቶች እና በሌሎች ማንነቶች መካከል አለመተማመንን ከፍጠራቸውም በላይ በጋራ ለመኖር የማያስችሉ የጥርጣሬ ምንጭም ሆነዋል፡፡

ያለፉት ሥርዓቶች የፈጠሯቸው ቁርሾዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱት ልዩነቶችና አለመግባባቶች በሃገራዊ ሰላምና ልማት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደ ወንድማማች ህዝብ የሃገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር አድዋ ላይ በጋራ ዘምተው ታላቅ አኩሪ ድል የተጎናጸፉና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ተብለው የሚጠሩ ጀግኖች ህዝቦች ናቸው፡፡

ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በርካታ ሃገራዊ ልማቶችን በጋራ ገንብተው ያጠናቀቁ የልማት አርበኞችም ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህንና ሌሎች በርካታ ሃገራዊ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች እስከ ዛሬ ድረስ የውስጥ ልዩነቶቻውን በምክክርና በንግግር ለመቅረፍ አልቻሉም፡፡

ዛሬ ላይ ግን መላው ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን በምክክርና በንግግር በመፍታት ለአፍሪካ ብሎም ለተቀረው አለም ምሳሌ የሚሆን ሌላ አዲስ ታሪክ ለመስራት ታላቁን ሃገራዊ የምክክር ጉባዔን በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይኛሉ፡፡

ይህ ሃገራዊ የምክክር ጉባዔ የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት ችግር ይቀርፋል ተብሎ የታመነበት ከመሆኑም በላይ ጠንካራ፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ከማውረስ ረገድም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review