AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን “ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” 3ኛ ዙር የክረምት ንቅናቄን አስጀምሯል፡፡
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ፤ በዘርፉ እየመጣ ያለው ለውጥ አመርቂ እና ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡
በአረንጓዴ የተዋቡ አካባቢዎች በስፋት እየተፈጠሩ መሆኑን በመግለጽ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ የሆነው የአካባቢ ጥበቃን ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል፣ ይህንንም ማላቅ እና ማሳደግ ተገቢነት አለው ነው ያሉት፡፡

የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ ኢትዮጵያ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምሳሌ የሆኑ ስራዎችን መስራቷ ኮፕ 32 የመሳሰሉ ጉባዔዎችን ለማስተናገድ ተመራጭ እያደረጋት ይገኛል ብለዋል።
የዘንድሮው ንቅናቄ ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ያለፉት ሁለት ንቅናቄዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን ጠቁመዋል።

የፕላስቲክ ብክለትን መከላከል፣ አደገኛ ቆሻሻ ወይም ኬሚካሎችን መከላከል እና የድምጽ ብክለትን መከላከል የንቅናቄው ማዕከል ሆኖ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ እሸቱ ለማ (ዶ/ር)፤ በንቅናቄው በአካባቢ ብክለት እና መከላከል ዙሪያ ለ1 ሚሊየን ዜጎች ግንዛቤ ይፈጠራል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የንቅናቄ ስራዎች በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውንም ገልጸዋል።

የህብረተሰብ ተሳትፎ ማሳደግ፣ ህግን ተግባራዊ ማድረግ እና ግንዛቤ መስጠትን መሠረት ያደረገ የግለሰብ የባህሪይ ለውጥ ማምጣት ከንቅናቄው የሚጠበቁ ጉዳዮች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በሃብታሙ ሙለታ