ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች- አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች- አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ

AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል።

አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ለሥራ ጉብኝት ከመጡት የአዘርባጃን ሪፐብሊክ የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ ጋር ባደረጉት ውይይት ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በባህልና በንግድ ያላቸውን ትብብርና ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ በተደረገው ውይይት ተገልጿል።

ከአዘርባጃን በተገኘው ልምድ በቅርቡ ተግባራዊ እየሆነ ያለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተቋማት ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የተገልጋዮችን እንግልት እያስቀረ መሆኑን አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማዕድንና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት በመግለጽ የአዘርባጃን ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገሪቱ የተካሄደውን ዲሞክራሲያዊ ምርጫና የሀገራዊ የምክክር ሂደትን ለልዑካን ቡድኑ እንዳብራሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን ለቱሪስቶች ምቹ እያደረገ እንደሚገኝና ከባኩ ከተማ ጋር በቅርሶች አስተዳደር፣ በቱሪዝምና ከተማ አስተዳደር ልምድ ለመውሰድ ፍላጎት መኖሩም ተገልጿል።

የአዘርባጃን ሪፐብሊክ የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እና በአዘርባጃን መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ እና ሁለንተናዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመው በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review