AMN ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
ዛሬ አዲስ አበባ አሮጌውን ሸማዋን እያወለቀች፣ አዲስ ብርሃን፣ አዲስ ተስፋ እና አዲስ ውበት በመጎናፀፍ ላይ ናት።
ጎዳናዎቿ አረንጓዴን እየለበሱ፣ ህንጻዎቿ በዘመናዊ ዲዛይን እየተቀየሩ ከምንም በላይ ደግሞ ለነዋሪዎቿ ህይወት መቀየር፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ አትኩራለች።
የከተማችን የሰው ተኮር ልማት ስራዎች በአስከፊ ሁኔታ የሚኖሩትን ወገኖች አስታውሰው፤ ለህፃናቱም፥ ለአዋቂውም፥ ለድሃውም፥ ለሃብታሙም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚያደርጉ ናቸው ።
ከነዚህ ሰው ተኮር ተግባራት ውስጥ አንዱ ትናንት በቆጥ ላይ ፣ በቆሸሸ ጎጆዎች፣ መፀዳጃ ቤት በሌላቸው፣ ክረምት ሲገባ በሚያፈሱ ቤቶች በኑሮም በጤናም እጅግ እየተቸገሩ ይኖሩ የነበሩ አቅመ ደካሞች እና የሀገር ባለውለታዎች ክብር ያለው ኑሮ እንዲኖሩ የመኖሪያ ቤት ለማቅረብ የተሰራው አኩሪ ተግባር በትልቁ ከሚጠቀሱት ውስጥ ነው ።

በተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት አረጋውያን ፥ ማህበራዊ ችግር ያለባቸው የሃገር ባለውለታዎች በቀን አንድ ጊዜ እየተመገቡ ይገኛሉ። በተመሳሳይ በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ቁርስ እና ምሳ ይመገባሉ። በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም እድሜአቸው እስከ ስድስት ዓመት የሆኑ ህፃናት እና አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ተጠቃሚ ሆነዋል።
ይህ ሁሉ ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ ከተማ፣ ንጹህ አካባቢ እና ተስፋ የተሞላ ህይወት የማኖር ተግባር ነው።
አዲስ አበባ እየተዋበች ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎቿንም እየቀየረች ያለች የብልፅግና ማሳያ ከተማ እየሆነች ነው! – የከንቲባ ጽ/ቤት