በአዲስ አበባ በአንድ ጀምበር ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል

AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ዘንድሮ ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለፁት ፣ በአዲስ አበባ በአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

ለምግብነት የሚያገለግሉ፣ ለውበት የሚሆኑ እና የደን ልማት ሽፋንን የሚያሳድጉ ችግኞች መዘጋጀታቸውንና የችግኝ መትከያ ቦታ መረጣ ሥራን ጨምሮ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ለከተማዋ ውበት፣ ለኢትዮጵያ እድገት እንዲሁም የደን ሽፋንን ለማሳደግ የሚደረግ ታሪካዊ እርምጃ በመሆኑ ሁሉም መሳተፍ እንዳለበትም አቶ ግርማ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብሩ 176 የሚሆኑ ቦታዎች እንደተለዩ እና የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን በሚጨምር መልኩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሚታየው ትጋት የአዲስ አበባ ከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ በዜጎች መካከል ያለውን አብሮነትና የሥራ ባህል የሚያሻሽል ነው።

እንደ ሃገር ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር ይከናወናል፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች በመላ ሀገሪቱ የተተከሉ ሲሆን ይሄም በርካታ ስኬቶችን አስገኝቷል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review