ለውጥ ዳር በመቆም ብቻ እንደማይሳካ በመገንዘብ እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቀረብ ብለው ይመልከቱ፤ ይጠይቁ፤ አብረው ይስሩ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

ለውጥ ዳር በመቆም ብቻ እንደማይሳካ በመረዳት፣ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እና ዘመኑን በመገንዘብ እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቀረብ ብለው ይመልከቱ፤ ይጠይቁ አብረው ይስሩ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሚዲያዎች ስላልነበሩ ብዙ ሰው አብዛኛውን መረጃ የሚያገኘው ከብሔራዊ ሚዲያ ነበር ብለዋል፡፡

በዚህም መረጃ በስፋት ሲሰራጭ እንዳልነበር በማስታወስ አሁን ላይ ብዙ ተናጋሪና ተንታኝ ያለበት ጊዜ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

በለውጥ ሂደት ውስጥ ብዙ ጉዳዮች ሊቀያየሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው ለውጥ የአንድ ሰሞን ድግስ ሳይሆን ረጅም መንገድ መሆኑን አምኖ፣ ራስን አስተምሮ ማስተካከል አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ጫና መቋቋም የሚሳናቸው ለጊዜያዊ ችግር ሲሉ ደግሞ ሸብረክ የሚሉ ሰዎች ጥጃው ሳይወለድ በረቱን እንደሚዘጋ ሰው ዓይነት ናቸው፤ ሂደቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈጸም ስላልሆነ ለርካሽ አላማ፣ ለርካሽ ጥቅም ሲባል ከቁም ነገር መጉደል አይሁንባችሁ ሲሉም ገልጸዋል።

ለወቅታዊ ችግር ሲባል ብርታት እና አቋም በማጣት የሀገርን ጥቅም በመወላወል ማሳጣት ጥቅም አለው ብየ አላምንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እና ዘመኑን በመገንዘብ ከታሪክ ቀኝ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሥራው እስከተሰራ እና ውጤት እስካለ ድረስ የሰው ልጅ የማየት የማመዛዘን አቅም እስካለ ድረስ እውነታው እየተገለጠ መሄዱ አይቀርም ብለዋል

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review