በመላው ኢትዮጵያ እስከ ቀኑ 10፡30 ድረስ ብቻ 278 ሺህ ሄክታር መሬት በችግኝ መሸፈን ተችሏል- የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ

AMN – ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ የዕለቱን የችግኝ ተከላ አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በመላው ኢትዮጵያ በተካሄደው የተቀናጀ አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እስከ ቀኑ 10፡30 ድረስ ብቻ 278 ሺህ ሄክታር መሬት በችግኝ መሸፈን ተችሏል ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ሰፊ ርብርብ የተነሳ እስከ 10፡30 ሰዓት ድረስ የታቀደውን የዕቅድ አፈጻጸም 96 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በዚህም 24.7 ሚሊየን የሚደርስ ህዝብ ከለሊቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በንቅናቄው ተሳትፏል።

በዕለቱ ለመትከል ከታለመው 800 ሚሊየን ችግኞች ውስጥ 765.7 ሚሊየን (96 በመቶው) ችግኞች ተተክለዋል። በሂደቱ 278 ሺህ ሄክታር ተጨማሪ መሬት በደን ተሸፍኗል።

ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተክሎች የጥምር ደንና የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ እንዲሁም ለአርሶ፣ ለአርብቶ አደሩ እና ለወጣቶች የኑሮ መሻሻል መሰረት የሚሆኑ ናቸው፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም ዛሬ የተከናወነው የችግኝ ተከላ ስራ የውሃ አካላትን ከደለል ማጽዳት፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከል እንዲሁም የኢትዮጵያን መልካም ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ የሚያደርግ ታላቅ ሀገራዊ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የቀሩትን ሰዓታት በመጠቀም የታቀደውን የ800 ሚሊየን ችግኝ ግብ ሙሉ በሙሉ ለማድረስ ህዝቡ የጀመረውን ርብርብ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review