አዲስ አበባ- ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት

AMN- ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት፡ በወንዝ ዳርቻና በመልሶ ማልማት ውብ፤ ጽዱና ማራኪ ከተማ ሆናለች፡፡ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና መልሶ ማልማት የከተማዋን ገጽታ ቀይሮታል፡፡

መንገዶች ከነሙሉ መሠረተ ልማታቸው ሰፍተዋል፣ ዘመናዊ ሆነዋል፡፡ ሰፊና ጥራት ያላቸው አስፋልት መንገዶች ምቹ የሆኑ ንጹህ የእግረኛ መንገዶች እና የብስክሌት መንገድ፤ የመብራትና የውበት ሥራዎችን አረንጓዴ ማረፍያ ቦታዎች በብዛትም ተሰርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞችንና አካባቢያቸው ከብክለት ጸድተው የዕረፍትና መዝናኛ ቦታዎች ሆነዋል፡፡የከተማችን አረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2.8 በመቶ ወደ 24 በመቶ አድጎ ውብ ማራኪ ከተማ ሆናለች፡፡

አዲስ አበባን በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽትም የሚዝናኑባት ከተማ ሆናለች፡፡አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሙዚየሞች፣ ፓርኮች፣ታሪካዊ ቅርሶች፣ የባህል ማዕከላት፣ ውብ ሆነው ታደሰዋል፡፡ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የሚካሄድባቸው የኮንፈረንስ ማዕከላትም ተገንብተዋል፡፡

ዛሬ አዲስ አበባ ለቱሪስቶች ረዘም ላሉ ቀናት እንዲቆዩ የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች አሏት፡፡

በዚህም የውጭ እና የሃገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የውጪ ቱሪስቶች ቁጥር ከነበረበት 123,489 ወደ 1.2 ሚሊየን አድጓል። የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ከነበረበት 4.1 ሚሊየን ወደ 1ዐ.5 ሚሊየን አድጓል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በተለየ ሁኔታ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ ተካሂደዋል፡፡ እየተካሄዱም ይገኛል፡፡ በእነዚህ ኮንፈረንሶች ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶች ከተማዋንና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ፡፡

ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች አዲስ አበባ ላይ ረዘም ላሉ ቀናት ይቆያሉ፡፡ አዲስ አበባ ዛሬ ከቱሪስት መተላለፊያነት፤ ወደ ቱሪስት መዳረሻነት እንዲሁም ተመራጭ የዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች ትገኛለች፡፡ ከንቲባ ጽ/ቤት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review