AMN – ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም
የአከራይ ተከራይ ውል በአከራይ እና ተከራይ መካከል ሕጋዊ እና መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር እያስቻለ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ላይ በየጊዜው የሚስተዋለውን ያልተገባ ጭማሪ ለመቆጣጠር ከሚወሰዱ እርምጃዎች አንዱ የሆነው የአከራይ ተከራይ ውል አፈፃፀም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ኤ ኤም ኤን ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል።
የጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ አብዱራዛቅ ጅማ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የተከራይን ማህበራዊ ሕይወት እና ገቢ በማረጋጋት እንዲሁም አከራዩ ንብረቱን በሕጋዊ እና ዋስትና ባለው መንገድ አከራይቶ እንዲጠቀም ከፍተኛ ጥቅም እያስገኘ ነው፡፡
ይህ ሥርዓት ነዋሪውን ካላስፈላጊ ወጪ የሚታደግ ሲሆን አከራዮችም ሕጋዊ የተከራይ መረጃ እና ዋስትና እንዲኖራቸው ትልቅ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
በክፍለ ከተማው ከ60 ሺህ በላይ የኪራይ ውሎች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ አብዱራዛቅ ፤ ተጠቃሚዎች ፈጣን አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉም መሶብ የአንድ ማዕከልን ጨምሮ በስምንት ማዕከላት አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በክፍለ ከተማው እየተሰጠ ባለው የአከራይ ተከራይ ውል አገልግሎት ተጠቃሚ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑን ገልጸዋል።
በወርቅነህ አቢዮ