የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተፈጥሮ ስነ-ምህዳራችንን በማስተካከልና በማልማት ኢትዮጵያን አረንጓዴ ምድር እያደረጋት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN- ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ከመትከል ወይም አካባቢን ከማስዋብ የዘለለ፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠበቅ፣ የማልማትና የዘላቂ ልማታችንን መሠረት የማጠናከር ስትራቴጂያዊ ሀገራዊ እርምጃ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ አረንጓዴ ዐሻራ – ተፈጥሮን ከመንከባከብ እስከ ሀገራዊ የምግብና ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የሚደርስ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም አቅማችንን ከማጠናከሩም በላይ፣ የተፈጥሮ ስነ-ምህዳራችንን በማስተካከልና በማልማት ኢትዮጵያን አረንጓዴ ምድር እያደረጋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትም ኢትዮጵያ በራሷ አቅምና በዜጎቿ የጋራ ጥረት የተፈጥሮ ሀብቷን መጠበቅና ማልማት እንደምትችል ያረጋገጡ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ረገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚሆኑ የወል ስኬቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለግብርና ምርታማነት፣ በምግብ ራስን ለመቻል እና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም ነው አረንጓዴ ዐሻራን የምግብና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ለማጠናከር ዋነኛ ዘላቂ ሀገራዊ የልማት ትኩረታችን ያደረግነው ብለዋል።

ይህ ትውልድ የተፈጥሮ ሀብቱን በመጠበቅና በማልማት የዚህ ዘመን መሻቱን ከማሟላት ባለፈ ለመጪው ትውልድ የበለጸገችና የማትበገር ኢትዮጵያን የማስረከብ ኃላፊነት አለበትም ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራና አስተማማኝ መሰረት ለመጣል ለዚህ ደግሞ የጀመርናቸውን የተቀናጁ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review