AMN- ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

ትውልድን በእሴት የመገንባትና ማህበራዊ አብሮነትን የማጠናከር ስራ ከሐይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው ከከተማው የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ አመራሮች ጋር እየመከረ ነው፡፡

ምክክሩ በ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ የሰላምና ማህበራዊ እሴት ግንባታ ስራዎች እና በ2019 በጀት ዓመት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሼህ አብዱልሃሚድ አህመድ፤ በ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በስኬት ተከብረው እንዲያልፉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠንካራ የአብሮነት ስራ ሰርቷል ብለዋል።
ጉባኤው ህፃናትንና አረጋውያንን በመደገፍ እንዲሁም የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ረገድ ማህበራዊ ግዴታውን በተግባር መወጣቱ ተጠቅሷል።
በቅርቡ በተጠናቀቀው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ ተቋማቱ ለሀገራዊ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውም ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ረታ እንደገለጹት፤ ቢሮው ትውልድን በእሴት የመገንባትና ማህበራዊ አብሮነትን የማጠናከር ስራ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት ሰርቷል።
የሃይማኖት ተቋማት ለትውልድና ለሀገር ግንባታ፣ ለህዝብ ትስስር እንዲሁም ለታሪክና ቅርስ ጥበቃ ዋልታና ምሰሶ ናቸው ያሉት አቶ ብርሃኑ ለሁሉም የምትመች ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥም የድርሻቸውን መጫወት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ