AMN – ነሐሴ 22/ 2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 76ኛው የዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ (RC76) ተሳታፊ ልዑካን በአዲስ አበባ የሚገኙ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችን እና የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።

ከየአፍሪካ አባል ሀገራት የተውጣጡ የጤና ሚኒስትሮች ፣ ከፍተኛ የዓለም ጤና ድርጅት አመራሮች፣ ከተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች የመጡ ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች እና በርካታ አለም አቀፍ ታዳሚዎች በጉብኝቱ ተሳትፈዋል፡፡
ጉብኝት፤ እንግዶቹ አህጉራዊ የጤና አጀንዳዎችን ከመምከር ባለፈ፣ ከተማዋ በቱሪዝምና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ለውጥ በቅርበት እንዲያዩት እድል እንደፈጠረላቸው ከአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በርካታ ሀገራት እንዲሁም ዓለም-አቀፍ ተቋማትን ያሰባሰበው ይህ ጉባኤ፤ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በብቃት የማስተናገድ አቅሟን ከማረጋገጡም በላይ፣ የቱሪዝም ፀጋዎቿን እና የልማት ስራዎቿን ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።