የጉሙዝ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ “ጓንዷ” በዓል በአዲስ አበባ ተከበረ

AMN – ነሐሴ 23/ 2018 ዓ.ም

የጉሙዝ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ የሆነው የ”ጓንዷ” በዓል “ጓንዷ ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ፣ ኢትዮጵያ በብዝሃ-ባህል ፀጋዎች የተገነባች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ይህም የጋራ መስተጋብርና የአብሮነት መንፈስ እንዲኖረን እንዲሁም በማንነታችንና በአገራዊ አንድነታችን እንድንኮራ እንደሚያስችለን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም የጉሙዝ ማህበረሰብ አኩሪ ታሪክና የዳበረ ባህልን በትውልድ ቅብብሎሽ መገንባት የቻለ ህዝብ መሆኑን አንስተው፣ ጓንዷ በህዝቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ባህላዊ ስርዓቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህን ባህላዊ ስርዓት አጥንቶ፣ መዝግቦ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አሳስበው፤ በዓሉ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብና አገራዊ ገጽታን ከፍ እንዲያደርግ ሁሉም አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ እና የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢንያም መንገሻ በበኩላቸው፣ ጓንዷ በጉሙዝ ብሔረሰብ ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር የደስታ፣ የሰላም፣ የምስጋና፣ የንጋት፣ የብርሃን እና የተስፋ ጮራ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

የጉሙዝ ብሔረሰብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ታደሰ ደሬሳ በበኩላቸው፣ በዓሉ የክረምትና የጨለማ ጊዜ አብቅቶ ብርሃንና ተስፋ የሚፈነጥቅበት፣ ከጨለማ የመውጣት፣ የነጻነትና ትንሳኤ ማረጋገጫ እንደሆነ አስረድተዋል።

አፈ ጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲህ ያለ በዓል እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የብሔረሰቡ ተወላጆች እና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች መገኘታቸውን ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review