የአደባባይ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ቱሪስቶች የሚመርጧት የአፍሪካ መዲና

You are currently viewing የአደባባይ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ቱሪስቶች የሚመርጧት የአፍሪካ መዲና

AMN – መስከረም 8/2019

ኢትዮጵያ የተለያዩ ህዝባዊ፤ መንግስታዊ፤ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላትን በአብሮነትና በአንድነት በማክበር የምትታወቅ አፍሪካዊት ሃገር ነች፡፡

በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶች ዘንድ የሚከበሩት አብዛኞቹ በአላት ያለምንም ልዩነት በአብሮነትና በወንድማማችነት የሚከበሩ መሆናቸዉ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡

በተለይ በአደባባይ የሚከበሩት በአላት የሃገር ዉስጥ እና የዉጭ ሃገራት እንግዶች በብዛት የሚሳተፉባቸዉ እንደ መሆናቸዉ መጠን በአሉን ለሚያከብሩትም ሆነ አካበበሩን ለሚመለከቱ ሰዎች የተለየ የደስታ ስሜትን የሚፈጥሩ ናቸዉ፡፡

በልዩ ልዩ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች፤ በህብር ባጌጡ አልባሳትና በተለያዩ ቋንቋዎች ማራኪ ዜማዎችና ዉዝዋዜዎች ታጅበዉ የሚከበሩት እነዚህ በአላት ከሃገር አልፈዉ የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ናቸዉ፡፡

በአላቱ ማህበራዊ መስተጋብሮችን የሚያጠናክሩና የሃገር ገጽታን የሚገነቡ ከመሆናቸዉም በላይ ለበርካቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ እና ኢኮኖሚን የሚያሳልጡ ናቸዉ፡፡

አብዛኞቹ በአላት የአፍሪካ መዲና በሆነችዉ አዲስ አበባ በድምቀት የሚከበሩ ሲሆን መዲናዋ እነዚህን በአላት በድምቀት ለማክበር በእጅጉ የተመቸች መሆኗን በርካታ ቱሪስቶች ይመሠክራሉ፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ በኮሪደርና ወንዝ ደርቻ ልማት አዲስ ገጽታን የተላበሰችዉ አዲስ አበባ ለጉብኝትም ሆነ የአደባባይ በአላትን በድምቀት ለማክበር ተመራጭ ሆናለች፡፡

በመዲናዋ የተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች፤ ታሪካዊ ቅርሶች፤ ፓርኮች፤ ፋዉንቴኖች፤ የመዝናኛ ስፍራዎች፤ ሆቴሎች፤ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለጉብኝትና ለአደባባይ በአላት ልዩ ገጽታን የሚያላብሱ ናቸዉ፡፡

ቱሪስቶች ሊጎበኟት ብቻ ሳይሆን ዉለዉ ሊያደርሩባት የሚመርጧ አዲስ አበባ አዲሱን አመት በደማቅ ሁኔታ ያከበረች ሲሆን በቀጣይ ቀናት መስቀልንና ኢሬቻን ጨምሮ የተለያዩ በአላትን ለማክበር በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡

በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎችም ለሃገር ዉስጥና ለዉጭ ሃገራት ጎብኝዎች የተሻለ አማራጭን የፈጠሩ ሲሆን ለኢትዮጵያ ማንሰራራትም ትልቅ መሰረት ሆነዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review