አዲሱ መንግሥት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ይመሰረታል – አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

You are currently viewing አዲሱ መንግሥት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ይመሰረታል – አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

AMN መስከረም 13/2019

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቅን ተከትሎ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የመንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

አፈ-ጉባኤው በመልዕክታቸው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 10 ሺህ 438 ዕጩዎች እንዲሁም ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተሳተፉበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ በስኬት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑንና ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ያስታወሱት አፈ-ጉባኤው፤ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመንም በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀምር በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 መደንገጉን አንስተዋል፡፡

እንደዚሁም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጥምር ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅና እንደሚመራ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም መሠረት መስከረም 25 ቀን የመንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ ለሥነ-ሥርዓቱ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የጠቆሙት አፈ-ጉባኤው፤ በሕዝብ የተመረጠው አዲሱ መንግሥት ቀጣዩን አምስት ዓመታት ሀገርና ሕዝብ የመምራት ኃላፊነት እንደሚረከብ አረጋግጠዋል፡፡

መጪው ዘመን የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የብልፅግና እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review