AMN – ጥቅምት 1/2019 ዓ.ም

በቀጣናው እየተካሄደ ያለው የፖለቲካ እና የጸጥታ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ጥቅም ለማስከበርና ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በቅርቡ በካይሮ፣ በአሥመራ እና በሕገወጡ የሕወሓት ቡድን በኩል የሚስተዋሉ ድርጊቶችና የተቀናጁ ጥረቶች የዚሁ አካል ናቸው።
የግብፅ የዘመናት ስግብግብ ፍላጎት፣ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እና የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ብሔራዊ ጥቅም ላይ በማተኮር ኢትዮጵያን በቋሚ የውስጥ ቀውስና በጫና ውስጥ በማጥመድ ሉዓላዊነቷን ማዳከም ነው። ይህ የራስ ወዳድነት አጀንዳ የሌሎችን ህልውና እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ፍጹም የሚክድ ነው።
በሌላ በኩል፣ አስመራ እና ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ከዚሁ መርህ አልባ የቀጣናው ሴራ ጋር በመተሳሰር፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የምታሳየውን እያደገ የመጣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ የበላይነት በቁጥጥር ስር ለማዋል የፈጠሩት የጋራ ግንባር ይታያል።
በሀገር ውስጥ ያሉ ሰብአዊና ማህበራዊ ልዩነቶች ሆን ብሎ በማቀጣጠል እና ግጭቶችን በማባባስ የፌዴራል መንግስቱን ትኩረትና አቅም የመበተን ስግብግብ ዓላማቸው፣ ለቀጣናው ሰላም ግድ የማይሰጣቸው ኃይሎች መሆናቸውን በግልጽ ያንፀባርቃል።
መንግሥት ይህን ስጋት ለመመከት እና ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በርካታ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችን ወስዷል።
ይህም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ አጋሮቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር የግብፅንም ሆነ የሌሎችን ታጣቂ ቡድኖች አሳሳች ትረካዎች እያከሸፈች እንድትቀጥል አስችሏታል።
የሀገር ውስጥ የልማት ሥራዎች እንደ ሕዳሴ ግድብ እና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ በማድረግ፣ የጠላቶች ዋና ዓላማ የሆነውን ልማትን የማስተጓጎል ሴራ ማክሸፍ ተችሏል።
የማንኛውንም አካል ትንኮሳ በብቃት መመከት የሚያስችል ዘመናዊ የመከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ መዋቅር በመገንባት የሀገርን ድንበርና ሰላም የማስጠበቅ ሥራም ተሠርቷል።
አላስፈላጊ ለሆኑ ትንኮሳዎች በችኮላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ጊዜን፣ ቦታን እና ሁኔታዎችን በጥናት በመምረጥ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ የበላይነትን የማረጋገጥ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን አደገኛ የሴራ መረብ ያከሸፈው በስሜት ሳይሆን በብስለት፣ በስትራቴጂያዊ ትዕግሥት እና በጥበብ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ሙሉ ያሸነፈችው በውስጥ ጥንካሬዋ እና በሕዝቧ አንድነት መሆኑን የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የካይሮ፣ የአሥመራ እና የሕገወጡ የሕወሓት ቡድን ጥምረት የቱንም ያህል ቢሸረብ፣ በብልህ አመራር፣ በጠንካራ ዲፕሎማሲ እና በመከላከያ ሠራዊት ዝግጁነት እንደ ሁልጊዜው እንደሚከሽፍም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በታምራት ቢሻው