AMN – ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ፣ በቅርስ፣ በትምህርት፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በደን ጥበቃ፣ እና በአጠቃላይ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተችው አስተዋጽዖ ምትክ የለሽ መሆኑን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፣ በ45ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ መክፈቻ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ ያላትን ዕምቅ ዐቅም በመጠቀም ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማጥፋት፣ ሰላምን ለማጽናት እና ሕዝቦችን ለማስተሣሠር ግንባር ቀደም ሚና እንደምትጫወት ተስፋ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
የሃይማኖት ተቋማት መንፈሳዊነትን ኃይል አድርገው ለሀገር ግንባታ በሚያደርጉት አስተዋጽዖ ሁሉ መንግሥት አብሯቸው ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡