AMN- ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

ከተማ አስተዳደሩ ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ በሚያደርገው ጥረት ሕብረተሰቡ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የሰብዓዊ ድጋፍ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች ተገንብተዋል።

ለሰብዓዊ ድጋፍ ተጠቃሚ ዜጎች የተለያዩ ግብዓቶችን በሕብረተሰብ ድጋፍ እና በመንግሥት በጀት የማሰባሰብ ስራም ተከናውኗል።
የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በከተማዋ የተገነቡትን የሰብዓዊ ድጋፍ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች እና ክምችታቸውን ጎብኝተዋል።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ተረጂነትን ለመቀነስ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።
የዚሁ ተግባር አካል የሆኑትን በከተማዋ የተገነቡ የሰብዓዊ ድጋፍ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች፣ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች የጎበኙ ሲሆን፣ ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር)፣ ተረጂነትን ለማስወገድ እና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እንደ ሀገር የተቀመጠው አቅጣጫ በከተማችንም ተግባራዊ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት የማሸጋገር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ጀማሉ፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የሰብዓዊ ድጋፍ ማከማቻ መጋዘኖች ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ በመጀመሪያው የአርበኝነት የኢትዮጵያ ነፃነት ተጠብቆ መቀጠሉን ጠቅሰው፣ በሁለተኛው የአርበኝነት ምዕራፍ ደግሞ የተሟላ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴቶችን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ሳሙኤል አሳስበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በየካ፣ በጉለሌ፣ በአራዳ፣ በቂርቆስ፣ በልደታ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች የተገነቡትን መጋዘኖች ጎብኝተዋል።
በዳንኤል መላኩ