ኢትዮጵያ ሰላሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ወደ ብልጽግና በቁጭት እየተሸጋገረች የምትገኝ ተምሳሌታዊ ሀገር ናት

You are currently viewing ኢትዮጵያ ሰላሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ወደ ብልጽግና በቁጭት እየተሸጋገረች የምትገኝ ተምሳሌታዊ ሀገር ናት

AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ሰላሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ወደ ብልጽግና በቁጭት እየተሸጋገረች የምትገኝ ተምሳሌታዊ ሀገር መሆኗን የህግ እና ሥራ አስተዳደር ምሁር ግርማ መኮነን(ዶ/ር) ገለጹ።

ግርማ መኮነን (ዶ/ር) ከኤ.ኤም.ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና ድንበር መዳፈር ፍጹም ከንቱና ሲከሽፉ የኖሩ ሙከራዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለየትኛውም ወራሪ ኃይል እጅ ሰጥታ የማታውቅ፣ በሉዓላዊነቷ የማትደራደር ጽኑ አቋም ባላቸው ጀግኖች ክብሯን ጠብቃ የኖረች ታላቅ ሀገር መሆኗን በአጽንኦት ተናግረዋል።

የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ለማተራመስ የሚደረጉ ውጫዊ ግፊቶች አዲስ ክስተት እንዳልሆኑ የገለጹት ምሁሩ ፤ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ታሪካዊ ግጭቶችና ጦርነቶች በኢትዮጵያውያን ጠንካራ ህዝባዊ ተጋድሎ እና በሀገር ወዳድ ክንደ ብርቱ ሰራዊቶቿ መክሸፋቸው ታሪክ የሚመሰክረው ሀቅ መሆኑን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ የዚህ ሁሉ መዋቅራዊ ውጥረት ዋና ጠንስስ ከካይሮ የሚነሳ መሆኑን እና ግብጽ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት መሆኗን አብራርተዋል።

ግብፆች በአባይ ወንዝ ጉዳይ ፣ በፖለቲካ ፣ በሃይማኖትና በማህበራዊ ጉዳዮች ኢትዮጵያን አዳክመው ለማቆየት የማያቋርጥ ስልታዊ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ግርማ መኮነን(ዶ/ር) አብራርተዋል።

ግብጽ ከጥንት ጀምሮ የወረሰችውን ያረጀ አመለካከትና የጥፋት አካሄድ በዘመናዊ የጂኦፖለቲካ ማዕቀፍ ለመድገም የምታደርገው የተናጠልና የህቡዕ ሙከራዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታና በሌሎችም አንጸባራቂ ሀገራዊ ድሎች መክሸፋቸውን አመላክተዋል።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ሥራዎች ባለፈ ወደ የልማት፣ የቴክኖሎጂና የብልጽግና ጎዳና በቁጭት እየተሸጋገረች የምትገኝ ተምሳሌታዊ ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ አህጉራዊ ጉዳዮች የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ፣ በውጭ ጠላቶቿ ከሚደረግባት ሴራዎች ይልቅ ለራሷ ህዝብ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና ዘላቂ ሰላም ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ዶ/ር ግርማ መኮነን በአጽንኦት ተናግረዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review