አዲስ አበባ: ወንዞቿን የምታድስ፣ ነዋሪዎቿን የምትጠብቅና ለተሻለ የወደፊት ከተማ መሠረት የምትጥል!

You are currently viewing አዲስ አበባ: ወንዞቿን የምታድስ፣ ነዋሪዎቿን የምትጠብቅና ለተሻለ የወደፊት ከተማ መሠረት የምትጥል!

AMN-ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም

ወንዞች የቆሻሻ መጣያ ሳይሆኑ፣ የሕይወት፣ የውበትና የዕድገት መሠረቶች ናቸው። አዲስ አበባም ይህንን እውነት በተግባር በማሳየት፣ ወንዞቿን ከቆሻሻና ከብክለት ለማላቀቅ፣ ነዋሪዎቿን ከጎርፍ አደጋ ለመጠበቅና የኑሮ ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችል ተግባራዊ ለውጥ እያከናወነች ትገኛለች።

ቀደም ሲል በቆሻሻ፣ በብክለትና በመጥፎ ሽታ ምክንያት ወደ ወንዞቻቸው ጀርባቸውን ሰጥተው የነበሩ የመኖሪያ ቤቶችና አካባቢዎች፣ ዛሬ እንደገና ፊታቸውን ወደ ወንዞቻቸው እንዲመልሱ ዕድል እየተፈጠረ ነው። የወንዝ ዳርቻዎችም ከብክለት የተላቀቁ፣ ለመዝናኛ፣ ለእረፍትና ለማኅበራዊ ትስስር የሚያገለግሉ ስፍራዎች እንዲሆኑ መንገድ እየተከፈተ ነው።

ይህ የልማት ሥራ የወንዝ ዳርቻዎችን በማስዋብ ብቻ አይገደብም። የነዋሪዎችን ጤናና ደኅንነት መጠበቅ፣ የተፈጥሮን ሚዛን ማስጠበቅ፣ የኑሮ ጥራትን ማሻሻልና ለቀጣዩ ትውልድ ንጹሕና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማን ማስረከብንም ያካትታል። በዚህ መልኩ የወንዞች መልሶ ማልማት የተፈጥሮን ክብር ከሰው ልጅ ደኅንነት ጋር የሚያገናኝ፣ ለዘላቂ የከተማ ልማት መሠረት የሚጥል አቅጣጫ ነው።

አዲስ አበባ ወንዞቿን ብቻ እያደሰች አይደለም፤ ከወንዞቿ ጋር ያላትን ግንኙነት፣ የነዋሪዎቿን የኑሮ ጥራትና የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ላይ ትገኛለች። ይህ የወንዞች ትንሳኤ የከተማዋን አዲስ ገጽታ ከመፍጠር ባለፈ፣ የነዋሪዎችን ከተማቸው ጋር ያላቸውን ትስስርም የሚያድስ ለውጥ ነው።

ይሁን እንጂ ይህ ለውጥ ዘላቂ እንዲሆን የከተማዋ አስተዳደርና ነዋሪዎች በጋራ መሥራት ይጠይቃል። ወንዞቻችንን ከቆሻሻ መጠበቅ፣ በዳርቻዎቻቸው ንጽህናን ማስጠበቅና የተመለሰውን የተፈጥሮ ሀብት በኃላፊነት መንከባከብ የሁሉም የጋራ ተግባር ነው። ለውጡ እንዲቀጥል የሁላችንም ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

ከቆሻሻ መጣያነት ወደ ሕይወት፣ ውበትና ተስፋ ምንጭ፤ የአዲስ አበባ ወንዞች ትንሳኤ እንደሚቀጥል የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review