AMN – ጥር 10/2017 ዓ.ም
ጥምቀትን ስናከብር፤ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን በማጎልበት፣ ኅብረ ብሔራዊነቱን በማጠናከር ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት እና ለሀገር ገፅታ ግንባታ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በማጉላት፣ ዉብ እና ደማቅ በሆነ ሁኔታ ሊሆን እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ጥምቀት በዓለም ካስተዋወቁን ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓሎቻችን አንዱ ነው ብለዋል።
የኅብረ ብሔራዊነት መገለጫ የሆነው የጥምቀት በዓል ኢትዮዽያዊያን በባህላዊ አልባሳት ደምቀዉ በተለያዩ ቋንቋዎች ሀይማታዊ እና ባህላዊ ትዕይንቶችን የሚያሳዩበት የእኛነታችን መገለጫ በዓል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዚህ በዓል ላይ የሚታየውን ሀይማኖታዊ ትዕይንት፣ ባህላችንን፣ ዉበታችንን፣ ድምቀታችንን፣ አብሮነታችንን እንዲሁም እሴቶቻችንን ተመልክተዉ ይደነቁበታል ብለዋል።
በዓሉ አብሮነት የሚጎለብትበት፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።