AMN-መጋቢት 1/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET-302 መጋቢት 1 ቀን 2011 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለመብረር በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በመከስከሱ በውስጡ የነበሩ ተሳፋሪዎች ህይወታቸው ማለፉን አስመልክቶ 6ኛ ዓመት የመታሰቢያ ሀውልት ምረቃ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡
በሥነ-ስርዓቱ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ አምባሰደሮች፣ የተለያዩ እንግዶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ለተጎጂዎች የመታሰቢያ ሀውልት ተቀምጦላቸዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ መጋቢት 1 ቀን 2011 የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ መቼም ሊረሳ የማይችል በልባችን ውስጥ ያለ ትልቀ ሀዘን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና ክስተቱ የአየር ትራንስፖርትን ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንድንሰራ ትምህርት የሰጠን ነበር ብለዋል።
ሚኒስትሩ ከዚህ አስከፊ አደጋ በኋላ የዓለም አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ደህንነትን ለማጎልበት፣ የአውሮፕላን ዲዛይን ለማሻሻል እና ቁጥጥር ለማጠናከር ጉልህ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዳስቻለውም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ በዚህ አደጋ ለተጎጂዎች ጥልቅ ሀዘናቸውን ገልፀው ለተጓጂ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህ አደጋ ቅድሚያ ለደህንነት ሰጥተን መስራት እንዳለብን ትምህርት ያገኘንበት ነው ብለዋል ።
አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ መታሰቢያ ሀውልቱ እስከሚሰራ ድረስ የአከባቢው ማህበረሰብ ላደረገው አሰተዋጽኦም ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።