AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ የማኅበረሰብ ጤና ተቋም የሆነውን የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል(Africa CDC) መቀመጫ በመሆኗ ክብር ይሰማታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በማዕከሉ ያሉት ላቦራቶሪዎች እና የምርምር አቅሞች በበሽታ መቆጣጠር ብሎም በወረርሽኞች እና ተላላፊ በሽታዎች ምላሽ በመስጠት ሥራ ከፍ ያለ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

ይኽ እድል ለሀገራችን የጤናው ዘርፍ ተመራማሪዎች እና ባለሞያዎች በአኅጉራዊ የምርምር ጥረቶች በመሳተፍ በዘመናዊ ላብራቶሪዎች እንዲጠቀሙም መንገድ ይከፍታል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አባል ሀገራት ከአጋሮች ጋር በመተባበር ይኽን ተቋም ማጠናከር ይገባናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአፍሪካ መሪዎች አኅጉራዊ የማኅበረሰብ ጤና ተቋማችን በመላው አኅጉራችን የጤና አገልግሎት በማሳደግ ላይ ተቀዳሚ በማድረግ ሥራ ላይ በሙሉ ኃላፊነት እንድንተባበር ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።