እንደ ብራዚል ያሉ የኢኮኖሚ መሰረታቸው ግብርና የሆነና ውጤታማ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ጋር ከፍ ባለ ትብብር በጋራ መስራት የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ ግብርና በጥናትና ምርምር ተደግፎ ከተተገበረ ሀገርን በአጭር ጊዜ የመለወጥ አቅም አለው ብለዋል፡፡
የላቲን አሜሪካዋ ብራዚል ባልተገደበ የምርት እድገትና ዘላቂ የግብርና ልማቷ ዛሬ ላይ ምርታቸውን ወደ ዓለም ከሚልኩት ሀገራት ቀደሚዎች ተርታ ላይ እንደምትገኝም አቶ ተመስገን ጠቁመዋል፡፡

ከሁለተኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መዋጋት እና የገጠር ልማት ጉባኤ ጎን ለጎን፣ የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ተግባራት የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡
ከዋና ከተማዋ ብራዚሊያ 1547 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ ወደምትገኘው ዝናብ አጠሯ ፔትሮሊና በመጓዝ ከ40 ዓመታት በላይ በዘለቀው የሀገሪቱ የግብርና ምርምር ኮርፖሬሽን (Embrapa) ቅርንጫፍ የጥናትና ምርምር ጣቢያ ስር የሚሰሩ የተለያዩ ተግባራትን ተመልክተናል ብለዋል።
በጉብኝታችንም የውሃ አሰባሰብ፣ አጠቃቀም እና አስተዳደር ስራዎችን፤ በረሃማነትን መቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ የዘር ንፅህና ያላቸው የእንስሳት መንጋዎችን፣ በመስኖ የሚለሙ ፍራፍሬዎችን፣ የተለያዩ የዓሣ ዝርያ እርባታዎችን ማየታቸውንም አመላክተዋል፡፡
እነዚህን ተግባራት ለመከወን የሚያስችሉ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ደጋፊ ቴክኖሎጂዎችን መመልከታቸውን የገለጹት አቶ ተመስገን፣ ኢትዮጵያ የግብርና እምቅ አቅሟን በፖሊሲ በተደገፈ፣ በልዩ አሰራርና ክትትል ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች በአጭር ጊዜ የላቀ ውጤት እያሳየች እንደምትገኝም ገልጸዋል፡፡
እንደ ብራዚል ያሉ የኢኮኖሚ መሰረታቸው ግብርና የሆነና ቀድመው ውጤታማ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ጋር ከፍ ባለ ትብብር አብሮ መስራት የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን፣ ያየናቸውን ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ቀምረን ስራ ላይ የምናውል ይሆናል ብለዋል።