በአዲስ አበባ ከተማ ለህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

You are currently viewing በአዲስ አበባ ከተማ ለህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

AMN-ሰኔ 11/2017 ዓ.ም

“ጥራት ያለውና አካታች የሆነን የህጻናት አስተደጋግ በአፍሪካ ለማምጣት የጋራ ትብብርን ማጠናከር” በሚል መሪ ቃል የአፍሪካ የህጻናት ጥበቃ ኮንፈረንስ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

ኮንፈረንሱን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአፍሪካ ህጻናትን የወደፊት ህይወት የተሻለ ለማድረግ መተባበር እና ትርጉም ያለው ተግባራዊ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ህጻናትን ማሳደግ የአንድ ወገን ግዴታ ብቻ ሳይሆን የጋራ ሀላፊነት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ነባሩን ህጻናትን በትብብር እና በህብረት የማሳደግ አፍሪካዊ ባህል አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም ነው ከንቲባ አዳነች የተናገሩት።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመኖሪያ መንደሮቻችን ምን እንደሚመስሉ መለስ ብለን መመልከት እና እያንዳንዱ አፍሪካዊ ህጻን በተለይም በመጀመሪያዎቹ የእድሜ ደረጃዎች ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲሁም ክብር አግኝቶ እያደገ ነው የሚለውን ማረጋገጥ ይገባልም ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች።

በጎርጎሮሳውያኑ 1990 የጸደቀው የአፍሪካ የህጻናት መብት ጥበቃ ቻርተር የቤተሰብ ፣ የባህል ማንነት እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ የህጻናትን ደህንነት እና እድገት ለመጠበቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው እንደሚያስቀምጥ የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች ይህም ለህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ለሚከናወነው ተግባር አጋዥ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የህጻናት መብት ጥበቃ ቀዳሚ ትኩረት ከሚሰጣቸው ብሔራዊ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባዋ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥም ዋነኛው ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረትም በአዲስ አበባ ከተማ ለህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ትኩረት መሠጠቱን ያነሱት ከንቲባዋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ግዜ እንመግባለን ይህም እርዳታን መስጠት ሳይሆን ክብርን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የዛሬ ሁለት አመት ገደማ በከተማዋ የተጀመረው ሁሉን አቀፉ የቀዳማይ ልጅነት እድገት መርሃ ግብር ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን ተደራሽ እንደሚያደርግ ያስታወቁት ከንቲባ አዳነች በፕሮግራሙ የህጻናት መዋያዎችን ለማስፋፋት፣ ሁሉን አካታች የመጫዎቻ ስፍራዎችን ለመገንባት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የወላጅ የምክር አገልግሎት ባለሞያዎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማሰማራት እንዳስቻለም አስታውቀዋል።

ይህ ርምጃም ህጻናት ከጨቅላነት እድሜያቸው ጀምሮ በአካልም በአእምሮም እንዲሁም በስነ ልቦና ጎልብተው እንዲያድጉ የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በከተማዋ በህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ላይ የሚሰራው ስራ በህጻናት ቀዳሚ ልጅነት እና መከላከል የሚቻል ሞትን ማስቀረት እና በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት እድሜ የተሟላ እድገትን መስጠት ከሚሉት የዘላቂ ልማት ግቦችን ከመሳሰሉ አለም አቀፍ የልማት አጀንዳዎች ጋር የተሳሰረ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review