አረንጓዴ ሸማን የለበሱ ሀገራት

You are currently viewing አረንጓዴ ሸማን የለበሱ ሀገራት

በፀሐይዋ ግለት ሁሉም እያረረ፣

ደገኛ፤ ቆለኛ፤   መባባሉ ቀረ፡፡

ያስብላል አንዳንዴ! ክረምትን በቲሸርት፣ ግንቦትን በጃኬት ሲሆን ነገሩ፡፡ የሰው ልጅ  ስነ ምህዳሩን እያዛባ፣ የሕልውናውን መሰረት እያራቆተ በአረንጓዴ ፀጋ የተሸለመችው ምድር ክብሯ እየረገፈ፣ ወዟ እየነጠፈ  በመምጣቱ የአረንጓዴ አሻራን ችላ ባሉ ሀገራት ላይ ገራገር ጠባይዋ  እየተቀየረ ነው፡፡

ምድር አረንጓዴ ልብሷ ሲገፈፍ ገላዋ በፀሐይ ወላፈን ሰርክ እየተለበለበ ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ውቅያኖሱ እየሞላ፣ በረዶው እየቀለጠ፣ በልቅ የጋዝ ልቀት የፀሐይ አደገኛ ጨረርን የሚጋርደው የደመናው ሸማ እየሳሳ ምድራዊ ወበቁ ለፍጡራን ሕልውና ስጋት እየሆነ መምጣቱ ምስክር አያሻም፡፡

ምድራችን ሚዛኗ ሲዛባ ደግሞ  ጤናማ ኢኮኖሚ እየራቀ፣ ድህነት እየመጠቀ፣ የግብርና ምርታማነት እያሽቆለቆለ፣ ስደት እያሻቀበ፤ ማህበራዊ ፍትህ እየጎደለ፣ የእርስ በርስ ግጭት እየጨመረ መጥቷል የሚሉም ብዙዎች ናቸው። በዚህም ድርቅ፣ በርሃማነት መስፋፋት፣ መሬት መሸርሸር፣ ጎርፍ፣ ርሀብ፣ እርዛት፣ የመሬት መንሸራተት… እና ቁጥር አልባ ጠንቆች ለዓለም ህዝብ መከራን እየጋበዙ ነው።

በዓለም አቀፍ እኩልነት እና በሥነ-ምህዳር ሽግግር ስራዎቹ እውቅናን ያተረፈው የዓለም ኢ-ፍትሐዊነት ላብራቶሪ ዳይሬክተር ሉካስ ቻንስል (ተባባሪ ፕሮፌሰር) እ.ኤ.አ  2020  Unsustainable Inequalities የተሰኘ ጥናታዊ መፅሐፍ አሳትመዋል፡፡ በዚህ ጥናታዊ ስራቸውም በማህበራዊ እኩልነት እና በአካባቢ መራቆት መካከል ያለውን ውስብስብ ግንኙነት መርምረዋል፡፡ መፍትሔዎቹንም አመላክተዋል፡፡

በዚህ መፅሐፍ ላይ በግልፅ እንደሰፈረው የባህር በረዶ ከአርክቲክ ዙሪያ ጠረፍ እየሸሸነው፡፡ በአልፕስ፣ በአላስካ እና በግሪንላንድ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ዝቅተኛ ላቲትዩዶች የተራራ ሰንሰለቶች የሚገኘው የበረዶ ግግርም በፍጥነት እየቀለጠ ነው፡፡

ይህም ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ በምድሪቱ ላይ እያስከተለ ይገኛል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ የሙቀት መጠን እንዲጨምር፣ የባህር ጠለል ከፍ እንዲል፣ የአየር ጠባይ እንዲለዋወጥ፣ እንዲሁም ለመተንበይ አዳጋች የሆኑ ሌሎች ከባድ የአየር ጠባይ የመለዋወጥ ሁኔታዎች እንዲከሰቱ ያደርጋል።  በሌላ በኩልም የዝናብ ስርጭት ለውጦች፣ የጎርፍ ክስተቶች፣ የድርቅ ወቅቶች፣ ተደጋጋሚ የሰደድ እሳት አደጋዎች፣ የውሃ አቅርቦት መመናመን እና ሌሎች ችግሮችንም ያስከትላል፡፡

የእነዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤትም የሰዎች ለችግር ተጋላጭነትን መጨመር፣ የግብርና ምርቶች መቀነስ፣ የምግብ ዋስትና አለመኖር፣ የውሃ አቅርቦት ችግር መባባስ፣ የስነ ምህዳር መጎዳት፣ እና የጤና ችግር መስፋፋትን እንደሚያመጣ ሉካስ ቻንስል (ተባባሪ ፕሮፌሰር)  በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ይላሉ  ዓለማችን የምታስተናግዳቸውን ተፈጥሯዊ አደጋዎች በዘላቂነት ለመቋቋም ከሚሰጡት ምክረ ሃሳብ ትልቁ አካባቢ መራቆትን መጠበቅ፣ የተራቆቱ የምድራችን ገጾችንም በአረንጓዴ ገጽታ መመለስ እና የደን ሽፋንን ማሳደግ አስፈላጊ ነው። 

የዓለም ሙቀት መጨመርን አስመልክቶ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ “በሃርቫርድ ጋዜጣ” ላይ በ2022 ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፡- ምድር ለሰው ትሰጠው የነበረው የሕይወት እስትንፋስ እንደ ሲኦል ወላፈን እየተጋረፈ ብዙ ነፍሳቶችንም እየቀጠፈ ነው፡፡ አስር ዓመታትን ባስቆጠረው በዚህ ጥናት ሰው ከተፈጥሮ ጋር የማይጠቅመው እልህና ጦርነት ውስጥ ስለመግባቱም ብዙ የተፈጥሮ ሀብት ውድመቶችን በመጠቃቀስ የችግሩን አሳሳቢነት በማስረገጥ የዩኒቨርሲቲው ጥናት አመላክቷል፡፡

ጠቢባን ከተፈጥሮ ጋር መስማማት ከራስ ጋር ከመዋደድ ይበልጣል ይላሉ፡፡ እውነትም የሰው ከተፈጥሮ ጋር ሳይስማማ እንኳን ከሌላው ይቅርና ከራሱ ጋር ሊግባባ አይችልም። የሰው ልጅ በምቾትና በሕይወት እንዲኖር ከምትረዳው ተፈጥሮ ጋር መስማማት አቅቶት በተለያዩ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የመከራ ጅራፍ ያለእረፍት መገረፍ ከጀመረ እልፍ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከስህተት የተማሩ ከተፈጥሮ ጋር ያበሩ ህዝቦች ግን አብዝቶ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በምድራችን፤ ላይቤሪያ፣ ማይናማር፣ አፍጋኒስታን፣ ሴራሊዮን እና አይቬሪኮስትን የመሳሰሉ ሀገራት አረንጓዴ ልብሳቸውን ከተገፈፉ የዓለማችን ሀገራት መካከል የሚመደቡ መሆናቸውን ከ (world population review.com) ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚሁ መረጃ መሰረትም  ሲዊዘርላንድ ከዓለማችን አረንጓዴ ፀጋን የለበሰች ቀዳሚ ሀገር ናት። ሲዊዘርላንድ የምድራችን አረንጓዴዋ ምድር የሚለውን ስያሜ እንዲህ በቀላል አላገኘችውም፡፡ በአጭር ጊዜም ሆነ በረዥም ጊዜ የሀገሪቷ ዕቅድ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ በዋናነት ይቀመጣል፡፡ በልዩ ትኩረትም ይሰራል። ዜጎቿ ስለ አረንጓዴ አሻራ ያላቸው ግንዛቤ ከፍ እንዲልም ብዙ ሰርታለች። ይህን በማድረጓም ያለማንም ወትዋችና ጎትጓች የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ የሲዊዘርላንዳውያን ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ መገለጫ ኩራታቸው ነው። ችግኝ መትከል፣ ተንከባክቦ ማሳደግና ተፈጥሮን  መጠበቅ ደግሞ የዚች ሀገር ዜጎች የጋራ ቋንቋ ነው።

ሲዊዘርላንድ ከዚህ ባሻገርም ተፈጥሮን ከሚበክሉ የሀይል ማመንጫዎች በመራቅ የፀሐይ፣ የንፋስ፣ የውሃ፣ የእንፋሎትና መሰል ንፁህ የሀይል ምንጮችን ትጠቀማለች፡፡ ይህንንም በማድረጓ የተረጋጋ እድገት የሚመዘገብባት፣ ጤናማና ረዥም ዕድሜ ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባት አረንጓዴዋ የምድራችን ቀዳሚ ሀገር ሆናለች፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ ከሲዊዘርላንድ በመቀጠል ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ፣ ማልታ፣ ሲዊድን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሉዘንበርግ፣ አየርላንድ እና  ፊኒላንድ እጅግ ጤናማ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው አረንጓዴ ለበስ ሀገራት ናቸው፡፡

ሀገራቱ ለዚህ የበቁበት ትልቁ ምስጢር ስለ አረንጓዴ አሻራ  ጥቅም የዜጎቻቸውን አመለካከት ከፍ በማድረጋቸው፣ ዘላቂነት ባለው መልኩ በአጭርና ረዥም ጊዜ ሀገራዊ ዕቅዶቻቸው የአረንጓዴ አሻራን ጉዳይ አካተውና ዜጎቻቸውን በነቂስ በማሳተፍ ጠንክረው በመስራታቸው፣ ታዳሽ የሀይል ምንጮችን  በመጠቀማቸው፣ መተኪያ የሌላቸውን የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን ተንከባክበው በመያዛቸውና የአካባቢ ልማት ስራዎቻቸው ትውልድ አስከባሪ ዘመን ተሸጋሪ እንዲሆኑ አስበው በመስራታቸው እንደሆነም መረጃው ያመለክታል፡፡

በጥንታዊው ታሪኳ ከሰው ልጆች ጦር ለመከላከል ታላቁን ግንብ በነጫጭ ድንጋዮች ገንብታ ድንበሯን በማጠር ዓለምን ያስደመመችው ቻይና፣ አሁን ደግሞ በአረንጓዴ ግንብ ከተፈጥሮ ጋር ለመወዳጄት የሚያስችላትን አዲስ ገድል እየፃፈች ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1978 ጀምሮ እየገነባች ያለችውን ግዙፍ የደን አጥር( አረንጓዴ ግንብ)፣ በሰሜናዊ ደረቃማ እና ከፊል ደረቃማ ዞኖች፣ የውስጥ ሞንጎሊያ፣ ጋንሱ፣ ኒንግዢያ እና ዢንጂያንግን የሚያካልል ነው። ይህ ፕሮጀክት የቻይና ህልውና ስጋት የሆነውን የጎቢ በረሃ መስፋፋትን እንደሚገታውም ይነገርለታል።

ቻይና የአረንጓዴ ግንብ መርሐ ግብር እ.ኤ.አ. በ 2024 ከ30 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን የደን ሽፋን በ1949 ከነበረበት 10 በመቶ ወደ 25 በመቶ ማሳደግ ችላለች።

የኪንግ አብዱላህ የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት ደግሞ ሳውዲን አረንጓዴ እያለበሰ ያለ ስልጡን መላ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2021 የተጀመረው ይህ ንቅናቄ የሀገሪቱ ህልውና ማስጠበቂያ የማዕዘን ድንጋይ ነው። ፕሮጀክቱ በደን ልማት፣ በብዝሀ ሕይወት ጥበቃ እና በልቀቶች ቅነሳ ላይ በማተኮር ሳውዲን በአካባቢያዊ ዘላቂ ልማት ላይ ዓለም አቀፋዊ መሪ ለማድረግ ያለመ ነው።

ከዋና ዋና ዓላማዎቹ መካከልም የደን ​​ልማት፣ በረሃማነትን ለመከላከል እና አረንጓዴ ሽፋንን ለማሳደግ 10 ቢሊዮን ችግኞችን በሳውዲ ምድር በመትከል፣ በ2030 የካርቦን ልቀትን በ278 ሚሊዮን ቶን መቀነስን የመሳሰሉ ወሳኝ ዓላማዎችን ያነገበ ነው፡፡

በሳውዲ አረቢያ አረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ  2024  ባሉት ዓመታት ብቻ ከ100 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ከ118 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ወደነበረበት ተመልሷል። ከዚህ ባሻገርም ታዳሽ ሀይልን የመጠቀም፣ ብዝሃ ህይወትን የመጠበቅ አቅም ከፍ እያለ እንደመጣም የሳውዲ መንግስት ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ከ2010 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በስፋት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሐ ግብር ተስፋ ሰጭ ለውጦች እያመጣ መሆኑን በርካቶች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡ በዚህና በተያያዥ ስራዎች እነ ሀሮማያን የመሳሰሉ ሀይቆች ዳግም ተወልደዋል፡፡ አቢያታና ሻላ ካንዣበበባቸው አደጋ ወጥተዋል፡፡ ተመናምነው የነበሩ ደናማ ስፍራዎችም ወደነበሩበት እየተመለሱ እንደሆነም የግብርና ሚኒስትር በተከታታይ የሚያወጣቸው ተጨባጭ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም በአስር ዓመቱ ስትራቴጂክ የልማት ዕቅዱ ካሰፈራቸው ስድስት አበይት ነጥቦች መካከል ከተፈጥሮ የተስማማ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት የሚለው አንዱ ጉዳይ  መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review