ቴህራን በስጋት ላይ እያለሁ በኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ አልደራደርም ባለችበት እና የአውሮፓ ሀገራት ሰላም ለማስፈን ጥረት ባደረጉበት ማግስት፣ ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው በሌላው አዲስ ጥቃቶችን ሰንዝረዋል።
8ኛ ቀኑን በያዘው የሀገራቱ ግጭት፣ ኢራን ወደ መካከለኛው እስራኤል ያስወነጨፈቻቸውን 5 ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ሁሉንም ማክሸፍ መቻሏን እና በአፀፋውም የኢራንን የሚሳኤል ማከማቻ እና የመሰረተ ልማት አውታሮችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት መሰንዘሯን እስራኤል አስታውቃለች፡፡
ሀገራቱ በፈፀሙት አዲስ ጥቃት እስካሁን የተመዘገበ የተጎጂዎች ቁጥር አለመኖሩን አር ቲ ኢ ዘግቧል፡፡
ይሁንና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል እንዳስታወቀው፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የኢራን ቁልፍ ባለስልጣናት እና የኒውክሌር ተመራማሪዎችን ጨምሮ 639 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ደግሞ 24 እስራኤላውያን መገደላቸው የዜና ወኪሉ አያይዞ ገልጿል፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የእስራኤል ጥቃት እስካልቆመ ድረስ ኢራን ከአሜሪካ ጋር በኒውክሌር መርሐ-ግብሯ ዙሪያ እንደማትደራደር አስታውቀዋል።
በትናንትናው እለት በኢራን እና አውሮፓ ህብረት መካከል በጄኔቫ በተካሄደው ውይይት ውጤት ላይ ባይደረስም፣ ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ውይይቶች ፈቃደኝነትን የሚያሳዩ ፍንጮች መታየታቸው በዘገባው ተካቷል።
በሊያት ካሳሁን