የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ጉዳዮችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ በሚያስችል አበረታች ሂደት ማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተያዘለት የገቢ ማሳደግ፣የዕዳ ሽግሽግ፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ማምጣት፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ ብሎም የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማ ከማድረግ እንዲሁም ሌሎች ዓላማዎቹን ከማሳካት አኳያ አመርቂ ውጤቶች ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሙ በውጤታማነት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ያነሱት የባንኩ ገዥ፤ በወጭ ንግድ፣በውጪ ምንዛሪ ክምችት፣ የዋጋ ንረትን በመቀነስ እንዲሁም በሌሎችም አመርቂ ውጤቶች እየታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙን ከሚደግፉት መካካል ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አፈጻጸም ከታቀደለት ግብ በላይ በማሳካት ላይ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የምግብ ነክ የዋጋ ንረት ከ12 በመቶ በታች መሆኑን ያነሱት የባንኩ ገዥ፤ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህንንም ለማሳካት ጥብቅ የሆነ የገንዝብና የፊስካል ፖሊሲ ይወሰዳል ያሉት የባንኩ ገዥ፤ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እሴት በመጨመር የንግድ ስርዓቱን ማሳለጥ እና ሌሎች እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ጠቁመዋል፡፡
በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በውጪ ምንዛሪ ስርዓት ውስጥ የተወሰደው እርምጃ ስርነቀልና ተመኑን በገበያ ከመወሰን ባለፈ በአጠቃላይ የውጪ ምንዛሪ ስርዓቱ የተሻለ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በማምጣት ላይ የሚገኘው ውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመሩን አንስተው፤ ባለፉት 11 ወራት የወጭ ንግድ አፈጻጸም ማደጉን ገልጸዋል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ በፊት የአገሪቷ የወጭ ንግድ ሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ይህ ዓመት በሚጠናቀቅበት ጊዜ የወጪ ንግድ ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የታቀደለትን ግቦች በማሳካት ላይ የሚገኘው በቂ ዝግጅትና ጥናቶች ተደርገው ወደ ስራ በመገባቱ መሆኑን አንስተው፤ ሪፎርሙ በርካታ ጉዳዮችን አሰባስቦ መተግበሩም ለውጤታማነት ማብቃቱን ተናግረዋል፡፡
ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ረገድ ትልቅ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከማድረግ ጎን ለጎን የፊስካል ፖሊሲና አዲስ የገንዘብ ፖሊሶዎችን እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡