ኢትዮጵያ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን በመገንባትና ዘመናዊ የአቪዬሽን ልማትን እዉን ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የአየር ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል ለመላዉ አፍሪካዉዊያንና አለም አቀፍ ተጓዦች ዋና መዳረሻ ሆኖ ለማገልግል ዓላማ ያለዉ ነዉ፡፡
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በፈረንሳይ እና በሞሮኮ በተካሄደው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ሰፊ ትኩረትን ስቧል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢንቨሰተሮች እና ፖሊሲ አውጪዎች በተሳተፉበት በዚህ አለም አቀፍ መድረክ ፕሮጀክቱ የትራንስፖርት ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር ቀጠናዊ የንግድ ትስስርን ለማሳለጥ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያለዉ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ዋንኛ አጀንዳ መሆን ችሏል፡፡
አፍሪካዊ የትብብር ልቀት ማሳያ የሆነውና በአጭር የግንባታ ጊዜ ዉስጥ የሚጠናቀቀው አዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ፣ እንዲሁም መካከለኛዉ ምስራቅ ሀገራት መካከል አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በፍጥነት እንደሚከፍት ይጠበቃል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአቪዬሽን እንዱስትሪን ለማጠናከር ትልቅ አቅም ያላት መሆኑን ያመላክታል፡፡ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አገልግሎቶች ከመስጠት ባለፈ አህጉራዊ የኢንቨስትመንት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፡፡
ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ጠንካራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠርና በሂደት ደግሞ አፍሪካዊ ውህደት እንዲጎለብት ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል ፡፡
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ሀገራዊ መንገደኞችን የማጓጓዝ አቅም 110 ሚሊዮን የሚያደርሰው ሲሆን፣ አየር መንገዱ እያደገ የመጣውን ቀልጣፋ የጉዞ እና የሎጂስቲክስ ፍላጎት እንዲሟላ ከማድረጉም ባለፈ የሀገሪቱን ዋና ዋና የልማት አጀንዳዎችን ከግብ እንዲደርሱ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ለዘመናዊ መሠረተ ልማት እና ለቀጠናዊ ትስስር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጎላ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ መላዉ አፍሪካዉያንን የሚያስተሳስር፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የሚያሳድግ፣ ብሔራዊ ኩራትን እና አህጉራዊ ትብብርን ከፍ የሚያደርግ ነዉ፡፡ – የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት