AMN- ህዳር 21/2018 ዓ.ም
“በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሰጥተዋል።
በዚሁ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ “ችግር ገፍቶ የሚጥለን ሳይሆን መድረስ ወደምንፈልግበት ገፍቶ የሚያስፈነጥረን ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
በችግር ትብታብ ታስረን እንዳንቀር፣ ተስፈንጥረን ወደምንፈልገው ለመድረስ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ዝላይ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዝላይ ትርጉም ግን ሰው ተኮር፣ ትውልድ መር መሆን ይገባዋል ብለዋል።

የመደመር ዝላይ ጽንሰ ሀሳብ ከቀዳሚው ጋር ያለንን ልዩነት ማጥበብ እና እመርታዊ ዕድገት ማምጣት ነው። የመደመራዊ ዝላይ መዳረሻ ደግሞ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።
ወደምንፈልገው ግብ ለመድረስ ሌሎች የረገጡትን ሁሉ መርገጥ አይጠበቅብንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ውጤት አይተን ከዚያ መማር ነው ያለብን ሲሉ ገልጸዋል።
ጊዜ የአርፋጅነት ፈተናን ማሸነፊያ መሆን አለበት። ከሀገርም ከሀገር ውጪም ከውድቀት መማር ቢያስፈልግም፣ እያንዳንዱን ዱካ መከተል ግን ውጤታማ አያደርግም ብለዋል።
ለዚህም ነባር አቅሞችን ወደ ውጤት መቀየር፣ አዳዲስ ዘርፎች፣ የመልማት አቅሞችና የገበያ እድሎችን በመፍጠር ያለን አቅም በማዘመን ወደ ዓለም ለመስፈንጠር መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከችግርና ፈተና ውስጥ ሊፈለቀቅ የሚችል ዕድል ካለ፣ ችግሩን ወደ ዕድል በመቀየር መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳለጥና ማረጋገጥ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
በበረከት ጌታቸው