የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት አድጓል

You are currently viewing የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት አድጓል

AMN- ህዳር 24/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣ ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዓለም አቀፍ ደኅንነት ትብብር ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሚስ ዋንግ ሊሲን ጋር በሽብርና በሌሎች ቀጠናዊና አህጉራዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በወይይታቸውም የቻይና እና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ደረጃ ማደጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገልጸዋል፡፡

‎ቻይና እየተገበረች ያለችው “ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” ፕሮጀክት እንዲሳካ ኢትዮጵያ በሴኩሪቲ ሴክተር ሪፎርም በገነባችው ዘመናዊና ጠንካራ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት አማካኝነት አስተማማኝ የደኅንነት ጥበቃ እያደረገች እንደምትገኝ ኮሚሽነር ጀነራል ተናግረዋል።

‎ ኮሚሽነር ጀነራሉ፣ ቻይና ትላልቅ ሁነቶችን በማዘጋጀት ያላትን ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ በመቅሰም እ.ኤ.አ. በ2027 የሚካሄደውን COP32 ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ እና እ.ኤ.አ በ2028 በኢትዮጵያ የሚካሄደውን 96ኛውን የዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤን ለማሳካት በትብብር አብረው እንደሚሰሩ በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል።

‎ሽብርተኝነትን እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን እንዲሁም የሳይበር ወንጀል እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል፤ በቴክኖሎጂ ሽግግር፤ በሰው ኃይል ግንባታ ላይ በትብበር አብረው ለመስራትን ተስማምተዋል፡፡

‎ኢትዮጵያ የቻይና የዓለም አቀፍ የህዝብ ደህንነት ትብብር ፎረም ዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በመሆኗ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኝነትንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጣች መሆኗ በውይይቱ ወቅት መገለጹን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለአዲስ ሚዲያ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

አምባሳደር ሚስ ዋንግ ሊሲን በበኩላቸው፣ ቻይና ለኢትዮጵያ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት በትምህርትና ስልጠና የሰው ኃይል ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በማቴሪያል ድጋፍ እና በልምድና ተሞክሮ ልውውጥ እያደረገች ያለችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አንስተው፣ በተለይም ሽብርተኝነትንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ከሁሉም የሀገራችን የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በቅርበትና በትብብር ለመስራት ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን በውይይቱ ወቅት አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review