የሰላም ስምምነቱን ምክንያት በማድረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የአማራ ፋኖ ህሕባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የፌደራል መንግስት ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ የዘለቀውንና በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ጥያቄዎችን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል።
የሰላም ጥያቄውን መሠረት በማድረግ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዘላቂ የሰላም ስምምነት ማካሄዳቸውን ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል በኩል የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ “ዕለቱ ለአማራ ክልል የሰላም በሮች የተከፈቱበትና በክልሉ ያለውን ግጭት ለማስቆም መሠረት የጣለ ስምምነት ነው” ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ከግጭት ጥፋት እንጅ የሚገኝ ጥቅም ባለመኖሩ ከሰላም ለማትረፍ በጋራ መሥራትና ዘላቂ ጥቅሞችን ማስከበር ይገባል።
በጫካ የሚገኙ፥ የሚታገሉና ጥያቄ ያላቸው ኃይሎችም ቢሆኑ የትግል ሁሉ መጨረሻው ውይይትና ድርድር በመሆኑ መንግስት የሰጠውን የሰላም አማራጭ ተከትለው ወደ ሰላም እንዲመጡ አቶ አረጋ አሳስበዋል።
ስምምነቱን በቀጣይነት ለማስፈፀም የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠዋል ያሉት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ተወካይ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ “ሕዝባዊ ጥያቄዎችንና መስተካከል የሚገባቸውን ሀሳቦች በውይይት ለመፍታት የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ወስኗል” ብለዋል። ሌሎች ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችም ይህንን መንገድ መከተል ይገባቸዋል ብለዋል ተወካዩ።
በንጉሱ በቃሉ